በምሥራቅ ወለጋ ዞን ታዳጊዋን የደፈረው በ12 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ – “ያስረገዛት በመሆኑ የተሰጠው ፍርድ በቂ አይደለም ” ሳጂን ጫልቱ ተሾመ

0
991

ነቀምቴ ህዳር 17/2010 የ14 ዓመት ታዳጊ አስገድዶ ደፍሯል የተባለው ግለሰብ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን በምሥራቅ ወለጋ ዞን የኑኑ ቁምባ ወረዳ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኦልያድ ለሙ እንደገለጹት ወንጀሉ የተፈጸመው በወረዳው ኮርቡ ሰቃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር መጋቢት 12/2009 ዓ.ም ነው።

ተከሳሽ ደምሰው ተስፋዬ ማሪ የተባለው ይሄው ግለሰብ የጎረቤቱ ልጅ በሆነችው ታዳጊ ላይ በዕለቱ  ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ ቤት ሰብሮ በመግባትና በማስፈራራት ጥቃት ፈጽሞባታል።

የወረዳው አቃቤ ህግም በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ መስርቶበት  ተከሳሹ  ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ በመቀበሉ ቀደም ብሎም የወንጀል ሪከርድ የሌለበት በመሆኑ እንደ አንድ ቅጣት ማቅለያ ተይዞለታል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የወረዳው ፍርድ ቤት በቅርቡ  በዋለው ችሎት ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው በማለት የእስራት ቅጣት ውሳኔውን  ማስተላለፉን የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።

የኑኑ ቁምባ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የሴቶች፣የህፃናትና ወጣቶች የሥርዓተ ፆታ የሥራ ሂደት አስተባባሪ ሳጂን ጫልቱ ተሾመ ” ግለሰቡ አስገድዶ ከመድፈሩም ባሻገር  ታዳጊዋን ያስረገዛት በመሆኑ የተሰጠው ፍርድ በቂ አይደለም “ብለዋል ።

የወረዳው ዐቃቤ ሕግ አቶ ረቢራ ተስፋዬ በበኩላቸው  የቅጣት ውሳኔው በቂና አስተማሪ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

Source: ENA