ሩት ፈይሳ የአለፈው አመት የ12 ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከመላው ኢትዮጲያ ሶስተኛውን ከፍተኛ ነጥብ ያመጣች እንስት

0
1823
  • ከስድስት መቶ በላይ ውጤት ካስመዘገቡ 23 የአዲስ አበባ ከተማ ተማሪዎች መካከል 21ዱ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው

በመዲናዋ በርካታ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ የግል የትምህርት መካናት ይገኛሉ። የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የመንግስትን ስርዓተ ትምህርት ከመተግበር አኳያ በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ወቀሳ ሲያሰማ ቆይቷል። ከሰሞኑም ችግሩ እንዳልተፈታና ከስርዓተ ትምህርቱ ወጣ ያለ ይዘት ያላቸው መፅሐፍትን እያስተማሩ እንደሆነ በመገናኛ ብዙሀን ዘንድ ሲስተጋባ ተመልክቻለሁ። በሌላ በኩል በብሔራዊ ፈተና ወቅት ፈተና መኮራረጅ በግል ትምህርት ተቋማት ዘንድ በስፋት ይስተዋላል የሚሉ ወገኖች አሉ። የግል ትምህርት ቤት የክፍያ ሁኔታም አስተማሪ ወላጆችን እያማረረ እንደሆነ ይሰማል።

“ወጣት ወይም ሶታ” ይለዋል ‘ብላቴና’ የሚለውን ቃል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ተቋም ያሳተመው መዝገበ ቃላት። ዮፍታሔና ሩት ብላቴናዎች ናቸው። ከ’ሶታነት’ ባሻገር ሁለቱም ቀለሜዋ ናቸው፤ ቀለሜዋ ብላቴናዎች። ዮፍታሔ ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 285 ሺህ 625 ተፈታኞች መካከል የከፍተኛው ውጤት ባለጸጋ ነው፤ ሩት ደግሞ (ከደብረ ማርቆሱ ባለምጡቁ አዕምሮ ዮሴፍ እናውጋው ቀጥላ) ሶስተኛ ደረጃን ተቆናጣለች። ሁለቱም የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው፤ ብላቴናዎቹ  ዘመነ አስኳላቸውን ከግል ትምህርት ቤቶች ሳያላቅቁ ነው እዚህ የደረሱት። እና ሁለቱ ብላቴናዎች ስለተነሱት ጉዳዮች ምን አስተያይት አላቸው? በትምህርታዊ ጉባኤ ላይ አግኝቻቸው ተከታዩን ብለውኝ ነበር።

በነገራችን ላይ ዮፍታሔ ዓይነ አፋር ሲሆን ሩት ደፋር ናት። ዮፍታሔ ጭምት ነው ወይም የመናገር ክህሎት አላዳበረም፤ በአንጻሩ ሩት ተናጋሪ ናት። ዮፍታሔ ልቦለድም ሆነ ታሪክ ማንበብ ላይ ብዙ አይደለም፤ ሩት ከልቦለድ ማንበብ አልፋ ግጥም መግጠም ይዳዳታል።

(ከሰሞኑ አሁን ያሉበትን የትምህርት ሁኔታ በስልክ አውርተናል)

 ቀለሜው ብላቴና

ኢዜአ፡- እንኳን ደስ አለህ! ቅድሚያ እስኪ ራስክን አስተዋውቀኝ!

ዮፍታሔ፡- ዮፍታሔ ባይሳ እባላለሁ፤ የተፈተንኩት ኦሜጋ ትምህርት ቤት ነው፤ እና ያመጣሁት 633 ነው።

ኢዜአ፡- ያንተ ውጤት ከተፈተኑ…ተማሪዎች ከፍተኛ መሆኑን ስትሰማ ምን አልክ?

ዮፍታሔ፡- እምም…(ሳቅ ብሎ ዝም)

ኢዜአ፡-እሺ አንተን ጨምሮ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ ከግል ትምህርት ቤት የተማሩ ተማሪዎች ናቸው። ለምን ይሆን?

ዮፍታሔ፡- እኔ እንጃ! የመንግስት ትምህርት ቤት ገብቼ ስለማላውቅ ስለዚህ መናገር ይከብደኛል።

ኢዜአ፡- የግል ትምህረት ቤቶች ተማሪዎች ከመንግስት ስርዓተ ትምህርት ወጣ ያለ ነገር ይማራሉ ይባላል እውነት ነው ዮፍታሔ?

ዮፍታሔ፡- እኛ የተማርነው ራሱ የመንግስትን ብሔራዊ ሥርዓተ ትምህርት ነው። ከዚያ ውጭ ብዙ የተማርነው ነገር የለም። ቢያንስ 98 በመቶ የሚሆነው ከመንግስት ሥርዓተ ትምህርት የወጣ ፈተና ነው፤ ፈተናው እንዳለ ማለት ነው። ስለዚህ ወጣ ያለ ነገር ብንማረም እንኳን ፈተና አይመጣም፡፡

ኢዜአ፡- በግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ የመኮራረጅ ባህል ተንሰራፍቷል ይባላል። በእናንተ ትምህርት ቤት እንዴት ነው?

ዮፍታሔ፡-ስለዚህ ይለፈኝ ( ሳቅ)

ኢዜአ፡- ከናንተ ትምህርት ቤት ካንተ ሌላ ከ600 በላይ ውጤት ያመጣ ተማሪ አለ?

ዮፍታሔ፡-ያለ አይመስለኝም፤ አልሰማሁም።

ኢዜአ፡- እሺ አመሰግናለሁ!

ዮፍታሔ፡- እኔም!

ቀለሜዋ ብላቴና 

ቀለሜዋ ብላቴናዎች

ኢዜአ፡- ለፈቃደኝነትሽ አመስግናለሁ! በመጀመሪያ እንተዋወቅ?

ሩት፡- ሩት ፈይሳ እባላለሁ፤ ከሳውዝ ዌስት አካዳሚ ነው የመጣሁት፤ ያመጣሁት ውጤትም 625  ነው።

ኢዜአ፡- ከስድስት መቶ በላይ ውጤት ካስመዘገቡ 23 የአዲስ አበባ ከተማ ተማሪዎች መካከል 21ዱ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው። ምን ይሆን ምስጢሩ?

ሩት፡- የአስተማሪዎቻችን የትኩረት መጠንና ለተማሪዎቻቸውና ለትምህርቱ ያላቸው ተነሳሽነትና  ጥረት ነው የሚመስለኝ። ማለት በመንግስት ትምህርት ቤቶችም አስተማሪዎች የሚኖሩ ይመስለኛል… ግን የግል ትምህርት ቤቶች ነገሮች የተመቻቹ ናቸው፤ ማለት ብዙ ፋሲሊቲዎች ይገኛሉ ከመንግስት ትምህርት ቤቶች አንጻር።

ኢዜአ፡- ከግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ ኩረጃው አዝማሚያ ከፍተኛ እንደሆነ ይታማል፤ ከዚያ በተጨማሪም ከስርዓተ ትምህርት ውጭ ይዘት ያላቸው መጽሐፍት ይሰጣሉም ይባላል። ሩት ምን አስተያይት አላት?

ሩት፡- እውነት ይመስለኛል፤እኛም የምናየው ነገር ነው። ውጤቱም ከፍ ያለው በኩረጃ ነው የሚለው ነገር ግን እውነት አይመስለኝም። ምክያቱም ምን ቢኮረጅ ያን ያህል ትልቅ ውጤት ማመጣት የሚቻል አይመስለኝም። የሆነ እውቀት ያስፈልጋል ያን ያህል ውጤት ለማምጣት። በኩረጃ ውጤት የሚያመጣ አለ፤ ግን ከመንግስትም ይኖራል ከግል ብቻ አይደለም፤ ኩረጃ ግለሰባዊ ነው።

ኢዜአ፡- ግል ትምህርት ቤት በመማርሽ የተለየ ነገር አገኘሁት የምትይው ነገር ምንድን ነው?

ሩት፡- ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ፋሲሊቲዎች አሉ። ሲቀጥል ዳይሬክተሮችም/ርዕሰ መምህራን/ አስተማሪዎቸም በስኬጁል ነው የሚመሩት። ማለቴ በጣም ስትሪክት ናቸው። ትምህርት ላይ አያላግጡም በስነ ስርዓት ነው የሚያስተምሩት። ገብቼ ባላውቅም ከሩቅ እንደምናየው መንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ ያን ያህል ስርዓቱን ጠብቆ የመሄድ ነገር አይታየም። ትንሽ ዲስ ኦርጋናይዝድ የመሆን ነገር ያለ ይመስለኛል።

ኢዜአ፡- ጥሩ፤ ሊያስተካክሉት የሚገባቸው ድክመቶች የምትያቸው ?

ሩት፡- ከክፍያ አንጻር በጣም የተወደደ ነው፤ በየዓመቱ መጨመር እኔ ትክክል ነው ብዬ አላስብም። ሲቀጥል በባህሪ በደንብ እንዲሰሩበት እመክራለሁ፤ በባህሪ ማለቴ ተማሪዎች በትምህርት ብቻ ሳይሆን በግብረ ገብነትም ብዙ ስነ ስርዓት ያላቸው እንዲሆኑ/ጎበዝ እንዲሆኑ እንዲረዳቸው ማለቴ ነው።

ኢዜአ፡- በነገራችን ላይ ውጤትሽ ከአገሪቱ ተፈታኞች ሶስተኛው ከፍተኛ ውጤት መሆኑን ስትሰሚ ስሜትሽ እንዴት ነበር? እንደዚህ አመጣለሁ ብለሽ ጠብቀሽ ነበር?

ሩት፡- ውይ! በጣም ነው ደስ ያለኝ(ወገቧን እየሰበቀች በደስታ)፤ በጣም ነው ደስ ያለኝ! እእ.. ይህን አመጣለሁ ብዬ ጠብቄ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ውጤቱ ሲመጣ ማስደንገጡ አይቀርም፤

ኢዜአ፡-የቀጣይ የሩት ጉዞ ወዴት ነው፤ የውጭ ትምህርት ዕድል ወይስ ቀጥታ ወደ አገር ቤት ዩኒቨርሲቲ?

ሩት፡-እእ… ህክምና ፊልድን ነው ልቀላቀል ያሰብኩት፤ ሜዲሲን ላጠና ነው የመረጥኩት፤ የውጭ ዕድል እስካሁን አላገኘሁም።

ኢዜአ፡- ግን እየፈለግሽ ነው?

ሩት፡- ሃሃሃ..ከተገኘ አልጠላም

ኢዜአ፣- እስኪ መልካም ዕድል፤የምጨምሪው ነገር ይኖር?

ሩት፡- በመጀመሪያ እግዚአብሄርን ነው የማመሰግነው ለዚህ ውጤት ስላበቃኝ። እናንተንም! (በሳቅ)

ዛሬ

ስደውል ስልክ አያነሱም ነበር። ከደቂቃዎች በኋላ ነው ያገኘኋቸው፤ ምክንያቱም ቤተ መፅሐፍት ተወሽቀው ከስነ ሕይወት ሳይንስ ጋር እየተወያዩ ነበር። ሁለቱ ቀለሜዋ ብላቴናዎች ዛሬ ላይ የህክምና ትምህርት ክፍል ተቀላቅለዋል። ዮፍታሔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሩት ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ። ዮፍታሔ በደቡብ ኮሪያና በአሜሪካ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የነጻ ትምህርት እድሎችን አመልክቶ እየተጠባበኩ ነው ብሏል። በተመሳሳይ የደራሲ አዳም ረታ አድናቂዋ ሩት የትምህርት እድል ማሰሷን አላቋረጠችም። እስከዛን ግን ሁለቱም ቀለሜዎች ቀለም ላይ ናቸው!!

ቀለሜዋ ብላቴናዎች

ምንጭ: ኢዜአ