የድምጻዊው ኃብተሚካኤል ደምሴ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

0
1377

Image result for habtemichael demissie

መስከረም 30/2010 የታዋቂው የባሕላዊ ሙዚቃ፣ መዲናና ዘለሰኛ ተጫዋች ኃብተሚካኤል ደምሴ ስርዓተ ቀብር በአስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።

ድምጻዊው ትናንት በደረሰበት የመኪና አደጋ ነው ሕይወቱ ያለፈው።

ትናንት ረፋድ አራት ሰዓት ላይ አበበ ቢቄላ ስቴድዬም አካባቢ ተሽከርካሪውን አቁሞ መንገድ በመሻገር ላይ እያለ ነበር የመገጨት አደጋ የደረሰበት።

በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ወደ ጳውሎስና አቤት ሆስፒታሎች ቢወስዱትም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።

በስርዓተ ቀብሩ ላይ የተነበበው የህይወት ታሪኩ እንደሚያመለክተው፤ ድምጻዊው ኃብተሚካኤል ከአቶ ደምሴ ጓንጉል እና ከወይዘሮ መነን አልዩ በ1944 ዓ.ም በቀድሞ አጠራር ወሎ ክፍለ ሀገር በለጋንቦ ወረዳ ደረባ በምትባል አካባቢ ነው የተወለደው።

ማሲንቆ በመጫወት በ1960ዎቹ መባቻ ወደ ሙዚቃው ዓለም ብቅ ያለው ኃብተሚካኤል፤ በርካታ ባሕላዊና በመዲናና ዘለሰኛ የተቃኙ ዜማዎችን ለሕዝብ አበርክቷል።

ከህይወት ታሪኩ መረዳት እንደሚቻለው ወደ ስራ ዓለም የተቀላቀለው በ1971 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ ስራውን የጀመረውም በአገር ፍቅር ቲያትር ተፈትኖ አንደኛ በመውጣት በባህል ክፍል ውስጥ ተመድቧል።

ኃብተሚካኤል በ1983 ዓ.ም “ወሎ ያፈራት” የተሰኘ አልበም ለህዝብ ካደረሰ በኋላ በተለያዩ መድረኮች በመጋበዝ ስራዎቹን አቅርቧል፤ አድናቆትም አትርፏል።

ኃብተሚካኤል ደምሴ 25 ያህል የሙዚቃ ካሴቶችን የሰራ ሲሆን በሙዚቃው ዓለም አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደነበርም ተወስቷል።

በባሕላዊ ዜማዎች ቅኝት የሚታወቀው ኃብተሚካኤል በተለያዩ ተውኔቶች ላይም ተሳትፏል። ከነዚህም መካከል ታጋይ ሲፋለም፣ መስታወትና ባልቻ አባ ነፍሶ ይጠቀሳሉ።

ድምጻዊ ኃብተሚካኤል የአገሩን ባሕላዊ ሙዚቃ ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ በኬንያ፣ ግሪክ፣ ሆላንድ፣ እንግሊዝና ጀርመን በመዘዋወር ባቀረባቸው ስራዎቹም አድናቆትን አትርፏል።

የአራት ወንድና የሦስት ሴት ልጆች አባት የሆነው ድምጻዊ ኃብተሚካኤል ደምሴ በደረሰበት የመኪና አደጋ  መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም በ66 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የድምጻዊ ኃብተሚካኤል ደምሴ ስርዓተ ቀብር በአስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሲፈጸም ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሙያ ባልደረቦቹና አድናቂዎቹ ተገኝተዋል።