አምስት ህጻናትን የሰረቀው ከባድ ቅጣት ተወሰነበት

0
738

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ ኢሉቻ ከሚባለው አካባቢ የካቲት 2009 ዓ/ም አምስት ህጻናትን ሰርቆ ለማዘዋወር የሞከረው በቁጥጥር ስር ውሎ ከባድ የእስር እና የገንዘብ ቅጣት የተወሰነበት መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ:: የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የቅጣት ውሳኔ መዝገብና የፖሊስ ምርመራ እንደሚያመለክተው ገነሞ ዋሪኮ የተባለው ወንጀለኛ ኢላቹ በሚባለው አካባቢ በመዘዋወር ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩትን እድሜያቸው ከ8 ዓመት እስከ 13 የሚሆናቸውን 5 ህጻናት በድብቅ በማሰባሰብ ለእያንዳንዳቸው ሰባት መቶ ብር በመስጠትና በማታለል ከአካባቢው ይሰወራል:: ህጻናቱንም በህዝብ ትራንስፖርት በመያዝ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ይጀምራል፤ ነግር ግን ከተነሳበት አካባቢ መድረሻው ላይ ሳይደርስ ዝዋይ ከተማ የህጻናቱ ሁኔታ ጥርጣሬ የገባቸው በአካባቢው የነበሩ ግለሰቦች ጥቆማ ለፖሊስ በማድረሳቸው ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር በማዋል ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ሲራሮ ወረዳ ይመልሰዋል:: የወረዳው ፖሊስም ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ለዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመላኩ ፍ/ቤቱ ማስረጃዎቹን በመመርመር ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ25 ዓመት ከባድ እስራትና የ200 ሺ ብር ቅጣት ወስኖበታል::