የ አ.አ. ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት ዳይሬክተር ዶክተር በላይ ሀጎስ እንደገለጹት 380 የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በድረ ገፅ ተለቀዋል

0
1719

29-6-2017

ዩኒቨርሲቲው 380 የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በድረ ገፅ ለቀቀ

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2009 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ትምህርት ጆርናል /መፅሔት/ ያሳተማቸውን 380 የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለተጠቃሚዎች በኢንተርኔት መልቀቁን አስታወቀ።

የጥናትና ምርምር ውጤቶቹ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 50 ዓመታት በአገሪቱ ያከናወናቸው ስራዎች ናቸው።

የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥናት ዳይሬክተር ዶክተር በላይ ሀጎስ እንደገለጹት ለተጠቃሚዎች በድረ ገጽ ይፋ የሆኑት የምርምርና ጥናት ውጤቶች በትምህርት ግብዓት፣ ሂደትና ውጤት ላይ ያጠነጥናሉ።

በተጨማሪም በስርዓተ ፆታ፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንጂነሪንግና በሂሳብ ትምህርቶች የተካሄዱ ጥናቶች መረጃዎችም ተካተዋል።

አብዛኞቹ የጥናትና ምርምር ስራዎች በዩኒቨርሲቲ መምህራን የተከናወኑ ሲሆኑ የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የስራ ውጤቶችም ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ትምህርት ጆርናል /መፅሔት/ ማኔጂንግ ኤዲተር ዶክተር ብርሃኑ አበራ በበኩላቸው ቀደም ሲል መፅሔቱ ከ300-500 ኮፒ እንደሚታተምና የተደራሽነትና ስርጭት ውስንነት እንደነበረበት አስታውሰዋል።

የህትመት ውጤቱ በድረ-ገፅ መሰራጨት የተደራሽነት ችግሩን እንደሚያቃልለው ጠቅሰዋል።

ጥናትና ምርምር ለሚያካሂዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ተማሪዎችና የበጎ ፈቃድ አጥኚዎች ማጣቀሻነት እንደሚያግዛቸውም አክለዋል።

በመፅሔቱ ታትመው የወጡት የምርምር ውጤቶች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለፖሊሲ ግብዓትነት ሲውሉ መቆየታቸው ተጠቅሷል።

አገልግሎት ላይ የሚገኘው የትምህርት ፖሊሲ በመፅሔቱ የወጡ የጥናትና ምርምር ሰነዶችን በከፍተኛ ሁኔታ መጠቀሙም ለአብነት ተነስቷል።

የጥናትና ምርምር ውጤቶቹን ejol.aau.edu.et በማለት ማግኘት የሚቻል መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

Source: ENA