የውጫሌ ውል የተፈረመበትን ቦታ ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋል 19 ሚሊዮን ብር ተመደበ- ለአፄ ምሊልክ ሀውልትስ?

0
948

ባህርዳር ጥር16/2009 የውጫሌ ውል የተፈረመበትን ቦታ ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋል 19 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ የሽዋስ ደሳለኝ ትናንት ለኢዜአ እንዳስታወቁት በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ የቱሪስት መስህብ ሃብቶችን አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው።

በተለይ የኢትዮጵያና የጣሊያን መንግስት የውጫሌ ውልን የተፈራረሙበት ”ይስማ ንጉስ” ተብሎ በሚጠራው ታሪካዊ ቦታ ላይ ቱሪስቶችን ለማስተናገድ የሚያስችል ግንባታ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

ግንባታውን በዚህ ዓመት ለማስጀመር ዝርዝር መረጃ የማሰባሰብና በተሰበሰበው መረጃ መሰረትም የግንባታ ፕላን ለማዘጋጀት በሂደት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ኘላኑ በመስህብ ስፍራው ደረጃውን የጠበቀ ሃውልት፣ ካፍቴሪያ፣ የስጦታ እቃዎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫና መሰል ግንባታዎችን እንዲያካትት ይደረጋል፡፡

ግንባታው አራት ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የሚከናወን ሲሆን  እስከ 2013 በማጠናቀቅ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ሃገራት ጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን  አቶ የሽዋስ አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል በግንባታው ዙሪያ የአካባቢውን ሕዝብ የማወያየት ሥራ የተከናወነ ሲሆን በቅርቡም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁራን ጋር ውይይት ለማደረግ መታቀዱን  አመልክተዋል።

በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግስት ሚያዚያ 24 ቀን 1881 ዓ.ም የተፈራረሙት የውጫሌ ውል 20 አንቀጾች ያሉት ሲሆን ”ይስማ ንጉስ” ወይም ”ስም ንጉስ” በመባል ይታወቃል።

የውጫሌ ውል በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ሮቢት ቀበሌ በሚገኝ ውጫሌ ሰፈር የተፈረመ ሲሆን ውሉን በጣሊያን በኩል ፒዮትሮ አንቶኔሊ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ አጼ ምኒልክ መፈረማቸውን የታሪክ መዝገቦች::

source: ENA