ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ በጋዜጠኛው ተረቱ

0
1057

መ/ር ዘመድኩን በቀለ

ለጋዜጠኛው ነጻ መባል የዲያቆን ዳንኤል ክብረት የመከላከያ ምስክርነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ እየተነገረ ነው ።


ረቡዕ ፣ ጥር 17 ቀን ጠዋት 4 ሰዓት አዲስአበባ – ኢትዮጵያ ።

ተከሳሽ አቶ ፍሬው አበበ ፦፣ ቅዱስነታቸው የሚመሩት ተቋም ከከሰሰኝ አይቀር ፍርድ ቤት ቀርበው በምስክርነት ይቆጠሩልኝ ። እንዲያውም በክሴ ጉዳይ ፥ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚታየውን የሙስናና ብልሹ አሠራር፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እና የመናፍቃን እንቅስቃሴ በስፋት መኖሩን ጭምር ያስረዱልኛል ። ምንም እንኳን ፓትርያርኩ ትልቅ የሃይማኖት አባት ቢኾኑም፣ በሕግ ፊት እንደ ማንኛውም ሰው በመኾናቸው ፍ/ቤት መቅረባቸው ለፍትሕ ሥርዓቱ ያላቸውን ከበሬታ ከማሳየት ባለፈ የሚነካባቸው ሞራል የለምና ቀርበው ይመስክሩልኝ በማለት ከቅዱስ ፓትሪያርካችን ሙግት ገጥሞ የከረመው ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ ዛሬ ከፍርድቤቱ ውሳኔ አግኝቷል ።

የሁለቱን ማለትም የከሳሽ የቅዱስ ፓትሪያርካችን የአቡነ ማትያስን እና የጋዜጠኛ ፍሬው አበበን ክርክርና ሙግት ሲመረምር የከረመው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ዘሬ ረቡዕ ፣ ጥር 17 ቀን ከጠዋት 4 ሰዓት ላይ ብዙ ፋይል በእጃቸው ተሸክመው የቀረቡት የቅዱስ ፓትሪያርኩ ነገረ ፈጅ በተገኙበት ጋዜጠኛ ፍሬው አበበና የዚህን የክስ ሂደት ፍጻሜ በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩትን ዜጎች በሙሉ ያስደሰተና ከክሱ በተጨማሪ የ100 ሺህ ብር ካሳ ከጋዜጠኛው ይጠብቁ የነበሩትን ቅዱስ ፓትሪያሪካችንን ቅር ያሰኘ ውሳኔ አስተላልፏል ።

የመረጃ ምንጮቼ ከዚያው ከቄራ የፍድ ችሎት ውስጥ ሆነው በቀጥታ ጉዳዩን እንዳስተላለፉልኝ ከሆነ ጋዜጠኛው የተከሰሰው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጻፈው ጽሑፍ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል ። ተከሳሹም ጸሐፊውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የመከላከያ ምስክር አድርጎ መቁጠሩም እንዲሁ ይታወቃል ። እናም ለጊዜው በአገልግሎት ምክንያት በሀገር ውስጥ ያሌለው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለጋዜጠኛው የመከላከያ ምስክርነቱን በጽሑፍ በመላኩና ፍርድቤቱም የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የመከላከያ ምስክርነትና ሌሎችንም በክሱ ሂደት የነበሩትን ጉዳዮች መርምሮ እንዲያውም የፓትሪያርኩን ጠበቃ ” አሠራራችሁን ግልጽ አድርጉ ። አስተካክሉም ” የሚል ገሳጼ በማቅረብ ተከሳሹን ጋዜጠኛ በነጻ አሰናብቶታል ።

በቀጣይ የቅዱስ ፓትርያርኩ በዛሬው የፍርድቤቱ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ በመጠየቅ በክርክሩ ይቀጥሉ ወይም አይቀጥሉ የታወቀ ነገርና ምን እንዳሰቡ ባይታወቅም የቅዱስነታቸው ጠበቃ ግን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አንገት መድፋታቸውንና መደንገጣቸውን በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞችና የመረጃ ምንጮቼ ነግረውኛል ። ለማንኛውም በታህሳስ 26/2009 ዓም የቅዱስነታቸውና የጋዜጠኛ ፍሬው የፍርድ ቤት ውሎ በተመለከተ በቀረብኩት መልእክት መጨረሻ ላይ እንዲህ ማለቴ ይታወሳል ።

ተዋህዶ ሃይማኖቴ ሆይ ፦ እግዚአብሔር ይሁንሽ ። አንገት ደፍተሽ ከመቀመጥ ተላቀሽ ቀና ብለሽ የምትሄጂበትን ዘመንም ያቅርብልሽ ።

ጋዜጠኛ ፍሬው ፦ ከገንዘብ ቅጣቱም ሆነ ከአካል እስራቱ እግዚአብሔር ይጠብቅህ ።

ቅዱስ አባታችን ፦ በእኔ በኩል ግድየለም ይቅርብዎ እንዳልል ስሜ ጠፍቷል ብለው ተነስተዋልና ማስቆሙ ይከብዳል ። አቤት ጉራዬ መቼም ሲበዛ ወገኛ ቢጤ ነኝ እኮ ። አሁን ማን ይሙት ደግሞ እኔን ብሎ መካሪ ። በዚህ ላይ የካሳ ብሩም 100 ሺህ ብር ነው ። እሱም ደግሞ ያጓጓል ። የጨነቀ ነገር ገጠመን እኮ ጎበዝ ። የሆነው ሆኖ እንደኔ እንደኔ ቅዱስነትዎ የተጀመረውን ክስ ቢያቋርጡና የጠፋውን ስምዎትን እንደምንም ተረባርበን ብናድስልዎ ። ገንዘቡንም ቢሆን በእያንዳንዳችን የሚደርስብን ተነግሮን የአቅማችንን ብናዋጣልዎና ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከውርደት ቢታደጓት መልካም ነው እላላሁ ። በማለት ነበር መልእክቴን የቋጨኹት ። ከዚህ ውስጥ ለጊዜው ጋዜጠኛ ፍሬው አበበን ” ከገንዘብ ቅጣቱም ሆነ ከአካል እስራቱ እግዚአብሔር ይጠብቅህ ።” ያልነው ተፈጻሚ ሆኖልናል ። ቀሪዎቹ ምኞታችንንም እግዚአብሔር እንደሚፈጽምልን ቅንጣት ታህል ጥርጥር አይኖረንም ።

ይህ የሚያጓጓም ደግሞም የሚያሳቅቅ ጉዳይ ለጊዜው በምእራፍ አንድ ላይ ታሪኩ በዚህ መልኩ የተቋጨ መስሎ ታይቷል ። በቀጣይ ድራማውን በክፍል ሁለት እንዲቀጥል የማስደረግ አቅሙ ያለው በቅዱስነታቸው እጅ ላይ ብቻ ነው የሚገኘው ። እኔ ግን ጉዳዩ በዚሁ ካላበቃ በቀር እስከ ፍጻሜው ድረስ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመከታተል እሞክራለሁ ። ለዛሬ አበቃሁ ።

ዘመድኩን በቀለ ነኝ ።
ጥር 17/2009 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ ።