ምስጢራዊቷ ማህደር ማርያም ደብር

0
1648
ማህደር ማርያም
Image: ማህደር ማርያም

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ደቡብ ጎንደር አቅንቶ ማህደረ ማርያም ደብር ገብቷል፡፡ ማህደረ ማርያም ማህደረ ታሪክ ናት ሲል ለዛሬ በታሪክ ጉልህ ስም ያላትን ጥንታዊት ደብር ያስጎበኘናል፡፡ ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ

ፋርጣ ነኝ፡፡ ከደብረ ታቦር 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋን ማህደረ ማርያም ፍለጋ፤ ጥንታዊት እና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ማህደረ ማርያም ከቅዱሱ ቤተሰብ ወደ ጣና የተደረገ ጉዞ ጋር ግንኙነት ያላት ስፍራ ናት፡፡

ማህደር ማርያም

በድርሳነ ዑራኤል ስሟ የተገለጸው ይህቺ ታላቅ ስፍራ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ቦታ የሚሰጣት ማህደረ ማርያም በ1553 ዓ.ም. በተራራዋ መካከል ላይ ቤተ ክርስቲያን ተመሰረተ፡፡ የተከሉትም ንጉስ ዐፄ ሠርፀ ድንግልና ባለቤታቸዉ እቴጌ ማርያም ስና ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያኗ አስተናነጽ የራሱ ታሪክና በርካታ መንፈሳዊ ክንዋኔዎች ያሉት ናቸው፡፡

ቤተክርስቲያኑ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ፀሎት ተደርሶ ቤተ ክርስቲያኑ ተባርኮ ታቦት ገብቶ ቅዳሴ ተቀድሶ ንጉሱና ንግስቲቱ በዚያዉ ስጋዉን ደሙን ተቀብለዋል፡፡ ይህንንም ሁሉ ከፈፀሙና ካስፈፀሙ በኋላ ንግስቲቱ እቴጌ ማርያም ስና በሞት ሲለዩ ከቤተ-መቅደሱ ዉስጥ ራሳቸዉ ባሰሩት ምስጢራዊ ምድር ቤት ተቀብረዋል፡፡

የብርቅዬ እና ጥንታዊ ቅርሶች መገኛዋ ማህደረ ማሪያም እንደ ስሟ ሁሉ ማህደር ቅርስ ልትባል የሚገባት ቦታ ነች፡፡ ማህደረ ማርያም የዐፄ ተክለ ጊዩርጊስና ካባና ቀሚስ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ስጦታዎች፣ የተለያዩ ልብሶች የወርቅ ጌጣጌጥ ያለዉ ካባና ሱሪ፣ የተለያዩ ንዋየ ቅድሳት የብር ከበሮ፣ የወርቅ ጽናጽሎች፣ የወርቅ ዋንጫ፣ የወርቅና የብር አክሊሎች፣ ከንግስት ዘውዲቱና ከአጼ ምኒልክ የተበረከተ አያሌ ቅርሶች፣ ከወርቅና ከብር ጌጣጌጦች የተሰሩ ካባዎች፣ የወርቅ ለምዶች፣ ከብር የተሰሩ መቋሚያዎችና ጽናጽል፣ ከአጼ ቴዎድሮስ የተሰጠ አንድ የወርቅ ጋሻ፣ የራስ ጉግሳ ዉሌ የወርቅ መስቀሎችና በየጊዜዉ የተበረከቱ የተለያ የእጅና የመጾር መስቀሎች ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የብራና መጽሐፍቶች የሚገኙባት ደብር ናት፡፡

READ  የአፍሪካ ዝሆኖች ምድር-ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ

ማህደር ማርያም

ክብና በድንጋይ የታነጸው ህንጻ ቤተ ክርስቲያን አስደናቂ መስኮትና በሮች ያሉት ኪነ ህንጻ አለው፡፡ በውስጡ የሚገኙ የበራፍ መቃኖች ላይ ያረፉት የሀረግ ጌጣጌጦች እና ቅርጻ ቅርጾች ታላቅ ጥበብ ይታይባቸዋል፡፡ ምሰሶዎቹ እጅግ አስደናቂ ናቸው፡፡ የግድግዳ ላይ የውስጥ ስዕሎቹም ቢሆኑ ከቃላት በላይ ናቸው፡፡

ማህደረ ማርያም ከምንም በላይ ለታሪክ ተመራማሪዎች የታሪክ ማህደር ናት፡፡ አወዛጋቢ ጉዳዮችን እልባት የሚሰጡ መረጃዎች የያዙ የነገሥታት ደብዳቤዎች ይገኙባታል፡፡ የራስ ጉግሣ ወሌን ልብ የሰረቀችው ማህደረ ማርያም በየዘመናቱ የተነሱ ነገሥታት ፍቅራቸውን የቸሯት ደብር መሆኗ ልዩ ያደርጋታል፡፡