Due to #AmharaProtest in Gonder, Ethiopian Airlines not flying

0
520

28-8-2016

የአማራ ክልል መንግሥት ችግሩ ከዚህ በላይ አይቀጥልም እያለ ነው

በአማራ ክልል ከወራት በፊት የተቀሳቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ አሁንም በመቀጠሉ፣ በተለይ በጎንደር ከተማ የተካሄደው ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ከተማዋን ከማንኛውም የዕለት እንቅስቃሴ አቅቧት ሰንብቷል፡፡

የጎንደር ከተማን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዲት የከተማዋ ነዋሪ፣ ‹‹እንኳን ሰው ወፍ ሳይቀር ነው ያደመው፤›› በማለት የተደረገውን የሦስት ቀናት የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ገልጸውታል፡፡

ከተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎችና የዓይን እማኞች ለማወቅ እንደተቻለው ከረቡዕ ነሐሴ 18 እስከ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው አድማ የንግድ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ መንግሥታዊ ተቋማት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና የተለያዩ የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መደበኛ አገልግሎት ሳይሰጡ ከርመዋል፡፡ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች የተሽከርካሪም ሆነ የእግረኛ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ሳይታይ መሰንበቱም ታውቋል፡፡

ከመንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት ያልተዘጉት የጎንደር ሪፈራል ሆስፒታልና የተወሰኑ ጤና ጣቢያዎች ብቻ መሆናቸውን የአንድ መንግሥታዊ ተቋም ኃላፊ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙ ግለሰብ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በቤት ውስጥ የመቆየት አድማው ከሁለት ሳምንት በፊት በሰላማዊ መንገድ ከተደረገው የአደባባይ የተቃውሞ ሠልፍ በኋላ ሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ነው፡፡

ምንም እንኳ ተቃውሞው በመንግሥት ላይ በወልቃይት ማንነትና በተያያዥ አስተዳደራዊ በደሎች የተነሳ ግፊት ለማምጣት ቢደረግም፣ አድማው የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየጎዳው መሆኑንም እየተነገረ ነው፡፡ የክልሉም መንግሥት ይህንኑ ያረጋገጠ ሲሆን፣ ተቃውሞውን ከዚህ በላይ እንዳይቀጥል ለማድረግ በፌደራል መንግሥት መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሐሙስ ነሐሴ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አመፁ የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየጎዳው መሆኑን በይፋ አረጋግጠዋል፡፡

ኅብረተሰቡ እያነሳቸው ላሉት ጥያቄዎች መርህን ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ‹‹በትክክለኛው›› መንገድ መልስ እንደሚሰጥ፣ ‹‹እየተለኮሱ ያሉት ግጭቶች እንዳይቀጥሉ በፌዴራል መንግሥት መወሰኑንና በፓርቲም ደረጃ ብአዴንና ኢሕአዴግም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፤›› ብለዋል፡፡

ተቃውሞው በጎንደር ብቻ ሳይወሰን በአካባቢውም እየተስተዋለ መሆኑንም ያረጋገጡት አቶ ገዱ፣ ‹‹በግጭቶቹ ምክንያት በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳይ ከማድረሱም በላይ፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ሥጋት መፍጠሩንና የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እያስተጓጎሉ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ሁከትና ግጭት በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ መመሰቃቀል ፈጥሯል ብለው፣ ከዚህ በላይ ኅብረተሰቡ በፍርሃትና በጭንቀት እንዲሸበብ አድርጓል ብለዋል፡፡ ክልሉ ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል አይፈቅድም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በተለይ በጎንደር ከተማና አካባቢው የንግድ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸው በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ ‹‹ከፍተኛ ሥጋትና ጫና›› እየፈጠረ እንደሚገኝ ጨምረው አስረድተዋል፡፡ ምንም እንኳ የጎንደሩ አድማ ቀደም ብሎ ለሦስት ቀናት የተጠራና ዓርብ እንደሚጠናቀቅ የተነገረ ቢሆንም፣ ለተጨማሪ ሁለት ቀናት እንደሚቀጥል ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ባለፈው ዓርብ ምሽት ለኅትመት እስከገባንበት ድረስ አድማው ይቀጥል አይቀጥል ለማወቅ አልተቻለም ነበር፡፡

በተያያዘ ዜናም የጎንደሩን አድማ ተከትሎ በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች ተመሳሳይ ተቃውሞዎች መካሄዳቸው ታውቋል፡፡ ነሐሴ 18 እና 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በፍኖተ ሰላም ከተማ የጎዳና ላይ ተቃውሞዎች መካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም በቡሬ ተመሳሳይ የተቃውም ሠልፍ መደረጉ ተሰምቷል፡፡

በባህር ዳር ከሁለት ሳምንት በፊት የተጠራ ሰላማዊ ሠልፍ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ መበተኑን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በፍኖተ ሰላም የተካሄደውንም ሕዝባዊ ተቃውሞ የፀጥታ ኃይሎች በኃይል መበተናቸውንና የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ እየተገለጸ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ መንግሥት ምንም ያለው ነገር የለም፡፡

በጎንደር በተጠራው ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ወደ ከተማዋ የሚገባም ሆነ የሚወጣ የሕዝብ ትራንስፖርት ባለመኖሩ፣ ወደ ከተማዋ ለሥራ ጉዳይ የሄዱ ግለሰቦች የትራንስፖርት አገልግሎት ባለማግኘታቸው ከእንቅስቃሴ መገደባቸውንም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ ባለፈው ዓርብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጎንደርና ባህር ዳር የሚያደርጋቸውን ዕለታዊ በረራዎች መሰረዙን ምንጮች ቢገልጹም፣ አየር መንገዱ ጥያቄ ቀርቦለት ማረጋገጫ ሊሰጥ አልቻለም፡፡

ነገር ግን ከጎንደር ምንጮች ሪፖርተር ለማወቅ እንደቻለው በአድማው ምክንያት አዘዞ አካባቢ የሚገኘው የአፄ ቴዎድሮስ ኤርፖርት የሕዝብ ትራንስፖርት በመቆሙ፣ መንገደኞችም ሆነ የኤርፖርቱ ሠራተኞች መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡

የጎንደር ከተማ በአገሪቱ በቱሪስቶች ከሚጎበኙ ከተማዎች በቀዳሚነት የምትታወቅ ሲሆን፣ ካለፉት ወራት ወዲህ የቱሪስት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ የቆመ መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡

በከተማዋ የሚገኙ የአንድ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት እንኳን የፈረንጅ ቱሪስት የአገር ውስጥ ባለጉዳዮች እንኳ ስለቀነሱ የመኝታ ክፍሎች ማከራየት አልተቻለም፤›› ሲሉ በአካባቢው የተፈጠረው አለመረጋጋት ያስከተለውን ተፅዕኖ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉ የንግድ ድርጀቶች፣ ትልልቅ ሆቴሎችና ካፌዎች ኅብረተሰቡ በብዛት የሚገለገልበትን በመለየት በወቅቱ እንዲከፍቱ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ያልሆኑ ድርጅቶችን ላልተወሰነ ጊዜ ማሸጉን ገልጿል፡፡ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየታቸውን፣ ገበያውን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሸማቶች ማኅበራትና የንግዱ ማኅበረሰብን ለማወያየት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ የተፈጠረውን ችግር ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መፍቀድ ችግሩን የበለጠ ማወሳሰብና በኅብረተሰቡና በክልሉ ላይ እየተፈጠረ ያለውን ሰላም የሚያደፈርስና የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ማባባስ በመሆኑ፣ ክልሉ ይህንን ማስተካከል የሚያስችል ዕርምጃ እንደሚወስድና ለዚህም ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

Source: Ethiopian Reporter