ከ1983 እስከ 2007 ዓ.ም በዐማራው ነገድ ተወላጆች ላይ ስለደረሰው የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል የጥናት ውጤት ማጠቃለያ ዘገባ [ሞረሽ ወገኔ]

0
1972
ሀ) መግቢያ
ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድነት ሃይሎችና በጎጠኞች መካከል የተካሄደው ፍልሚያ ፤ በጎጠኞች አሸናፊነት ከተደመደመ ወዲህ እራሱን የቻለ የፖለቲካ ውጥንቅጥ እስከትሎ እንደሚመጣ የተገመተ ቢሆንም ወደ ዘር ማጥፋትና ማጽዳት ያመራል ብሎ የተነበየ ከቶ አልነበረም። የጎጠኞች ያልተጠበቀ ድልና እሱንም ተከትሎ የመጣው ስካር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዐማሮችን ደም አፍሷል፤ እያፈሰሰም ነው። ክረምትና በጋ ፣ ቁር ፣ ሃሩር ሳይለይ ሌት ተቀን ሳይባል፤ ምስራቅ ይሁን ሰሜን ሳይል ፣ ክብረ በአልና የሰርክ ቀናት ሳይለይ ፣ ከ1983 እስከ ያዝነው 2008 ዓ.ም የዐማሮች እጣ ፋንታቸው መፈናቀልና መገደል ሆኗል። እንደከብት የታረዱት ፣ እሳት የበላቸው ፣ በግፍ ያለቁት በሺዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ዐማሮች ደም በኢትዮጵያ ምድር በአራቱም ማእዘናት በመጮህ ላይ ነው!
ከተለያዩ ባህርታዊ/መድብለ ባህል/ አገሮች ልምድ እንደታየው ፣ የአናሳዎች ፖለቲካ መዘዙ ትላልቅ ነገዶችን የሥልጣናቸው የስጋት ምንጭ አድርገው መመልከታቸው ሲሆን ፣ የትግሬ-ወያኔዎች ሥልጣን እንደያዙ የንጹሃን ዐማሮችን ደም በማፍሰስ የከፋፍለህ ግዛው ተግባራቸውን ጀመሩ። እነሱም ብቻ ሳይሆኑ ፣ በወቅቱ ከወያኔ ጋር የማያዛልቅ የፖለቲካ ጋብቻ የፈጸመው ኦነግ የወያኔዎች ቀኝ እጅ በመሆን ፣ በዐማራው ላይ የፈፀመው ወንጀል በታሪክ የማይረሳ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ፣ የወያኔዎችን የአናሳዎች ፖለቲካ የሎሌነት ሥራ ሰርቶ ለራሱም ሳይቀናው ከመድረክ ተገፍትሮ ቀርቷል። ኦህዴድ የተባለው ሌላው ተረኛ የወያኔ ተለጣፊ ድርጅት እስካሁን የዐማራን ሕዝብ እየገደለና እያፈናቀለ ይገኛል። የትግራይ ሕዝብ ሃርነት ግንባር ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና በወቅቱ አብሮት የቆመው «ጃራ» እያለ እራሱን የሚጠራው እስላማዊ ጽንፈኛ ቡድን ፣ እንዲሁም የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የዐማራውን ሕዝብ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል እንዳቀነባበሩ እንደመሩና እንዳስፈጸሙ ጥናቱ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል።
እነዚህ ከወያኔ ያላነሱ ዘረኛ ድርጅቶች የተሰራውን ወንጀል ሁሉ በወያኔው የአናሳ መንግስት ሲያሳብቡ ይሰማል። ይሁን እንጂ ይህ ወንጀል «ወያኔ ነው እንዲህ ያደረገው» በሚል ቀላል ማሳበቢያ የሚያመልጡት ጉዳይ ከቶ ሊሆን አይችልም። ወንጀል ተደብቆ አይቀርም። እንኳን የ25 አመት ታሪክ ይቅርና የሁለተኛው አለም ጦርነት የናዚ እና ፋሽስት ነፍሰ ገዳዮች አደን እስካሁን አልቆመም። በወረንጦ መለቀማቸው ቀጥሏል።
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት፤ የዐማራውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል በተመለከተ ዝርዝር ጥናት አስጠንቶ ማቅረቡንና የጥናቱንም አጠቃላይ ዘገባ የመጀመሪያ ክፍል ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ጥናቱ ዝርዝርና ትልቅ መድብል የያዘ ሲሆን በአንድና ሁለት መግለጫዎች ብቻ ጭብጡንና ድርጊቱን ለማስተዋወቅ ያዳግታል።
ይህንኑ የዐማራውን እልቂት አስመልክቶ ላለፉት 25 አመታት በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ፣ በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የተለያዩ ዘገባዎች ቀርበዋል። ይሁን እንጂ ይህንን በሕዝብ ላይ የተፈፀመ ትልቅ ወንጀል በመጣጥፎችና በመግለጫዎች ብቻ የጥፋቱን ደረጃ፤ ምክኒያቱን፤ ተዋናዮችን ወዘተርፈ በዝርዝርና በተጨበጠ መረጃ ማሳየት አይቻልም። ስለሆነም ይህንን የአለምአቀፍ የጥናት ስልቶችን የተከተለና ደረጃውን የጠበቀ ፣ መረጃው ታአማኒነት ያለው በርካታ ናሙናዎችን ያካተተ ታሪካዊ-ዳራ ያለውን ይህን ጥናት ማሰናዳት ግድ ብሏል። አንዳንዶቹ እዚህ ጥናት ውስጥ የተካተቱት ወንጀሎችም በፍጹም ተደብቀው የነበረና በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ሆነ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ያልተዳሰሱ ናቸው። ለምሳሌ በጥናቱ ውስጥ በእቅድ ተይዞ የነበረው ምሥራቅ ሐረርጌ ብቻ ነበር። ዳሩ ግን የምስራቅ ሐረርጌን ወንጀል ለማጥናት ሥራው ሲካሄድ ምዕራብ ሐረርጌ ላይ ከፍተኛ ወንጀል እንደተፈፀመ ከተሳታፊዎች ጥቆማ በመስጠቱ ስለዚህ ጥናቱ ምዕራብ ሐረርጌንም ማካተት ግድ ሆነበት።
ይህ በሞረሽ-ወገኔ አመራርና የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ ጥናት አደጋውን/ወንጀሉን ከሰሙ ሁለተኛና ሶስተኛ ክፍሎች በቅብብሎሽ መረጃ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ፣ ከእሳቱና ከእልቂቱ በተአምር ከተረፉና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በግፍ ካለቁባቸው ቤተሰቦች አንደበት የተሰበሰበ ፣ በማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ቋንቋ አንደኛ ደረጃ መረጃ /PRIMARY DATA/ ላይ የተመሰረተ ነው። በመጀመሪያ ባወጣነው የማጠቃለያ ዘገባ ላይ በግርድፉ፤ የጥፋቱን ደረጃና ስፋት የወንጀሉን አስፈጻሚና ፈጻሚዎች ፣ አፈጻጸሙንና የተፈጸመበትን ስፍራና ወቅት ፣ ወዘተርፈ አሳልጠን ማቅረባችን ይታወሳል።
በጥቅል የአማራው እልቂት በሚከተለው መንገድ የተፈጸመ ነበር፦
የጠላት ጦር ምሽግ ይመስል የደሆቹን ዐማሮች የሳር ጎጆ ቤቶች ፣ ነዋሪዎቻቸው ከውስጥ እያሉ የታመሙ አረጋውያን በመደቦቻቸው ላይ ተኝተው ባሉበት በከባድ መሣሪያ (ላውንቸርና ሞርታር) እንዲጋዩ ተደርጓል፤
እምቦቆቅላ ህፃናት ከእናታቸው አንቀልባ እየተመነጨቁ ወደ እቶን እሳት ተጥለዋል፤
አዛውንቶች እንደእርድ ከብት በሜንጫ ፣ በሰይፍ ፣ በቢላዋ እንዲሁም በገጀራ አንገታቸው እየተቀላ በየጥሻው ወድቀው ቀርተዋል፤
ያለ እዳቸውና ያለጥፋታቸው ገላቸው እንደ ቤተሙከራ መመራመሪያ አይጥ እየተተለተለ ሲቃና ጣር ሳይለያቸው ለዘለአለም እንዲያሸልቡ ተፈርዶባቸዋል፤
«ሁሉን በቃኝ» ብለው ገዳም የገቡት መንፈሳዊ አባቶች ሳይቀሩ በዐማራነታቸውና በእምነታቸው ብቻ በገደል እየተምዘገዘጉ እንዲከሰከሱ ተደርገዋል፤
ሰብአዊነት ትርጉም እስኪያጣ ድረስ እድሜ ፃታ ሳይለይ፣ በኋላቀሮች ስለት ቃላት ለመግለጽ በሚያዳግተው ሁኔታ ሕይወት እንደቅጠል ረግፏል፤
ባሎቻቸው የፍጥኝ ታስረው ፣ እማወራዎች ዘመን ባጠገባቸው ወጠጤ ጎሰኞች ክብረስብእናቸው ተዋርዷል፤ የኋላ ቀሮች የፋስካ ፍሪዳ ሆነዋል፤ ብዙም ብዙም የማይረሳ ወንጀል ተፈጽሟል፤
የአጋዚ ክፍለ ጦር ጎንደር ውስጥ ብቻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመንፈሣዊ አገልግሎት ላይ የነበሩ 65 ሰዎችን ባንዴ ፈጅቷል፤
እዚህ ላይ አንድ ግልጽ ማድረግ ያለብን ነገር ፣ ይህንን ወንጀል ሲፈፀም ትእዛዝ የሰጡ ፣ በቦታው ተገኝተው ያስፈፀሙ ዋና ዋና ነፍሰገዳዮች ሥም ዝርዝር ፣ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ በምን ተግባር ላይ ተሰማርተው እንዳሉና የትም እንደሚኖሩ ፣ መረጃቸውና የአንዳንዶቹ ፎቶግራፎችም ሳይቀር በጥናቱ ውስጥ ተካትቷል። ይህንን ዝርዝር መረጃ ይፋ ማድረጉ ለወንጀለኞች ቀላል መሽሎኪያ መንገድ ማዘጋጀት ስለሚሆን ይህንን ከማድረግ ተቆጥበናል። እጅግ በረቀቀ መንገድ ይህንን ጉዳይ የያዘው አጥኚው ቡድንም አንዳንድ ስልጣን ላይ ያሉ ነብሰ ገዳዮችን ለማነጋገር ሞክሮ ባይሳካለትም ለወደፊት በቀላሉ ሊደረስባቸው በሚያስችል ሁኔታ ዝርዝር መረጃ አጠናቅሮ ይዟል። አንዳንዶቹ ወንጀለኞች ዛሬ በሕይወት የሉም ከፍርድ ግን አያመልጡም። እልቂቱን በበላይነት የመሩ ጥቂቶቹ ዋና ዋና ተዋኒያን ሥም ዝርዝር ተጠናቅሯል። በዚህ ቀጣዩ ዘገባ ደግሞ አንዳንድ ተጨባጭነት ያላቸውንና የምስል ማስረጃዎችን ጭምር የጥናት ውጤቶችን ነቅሰን አቅርበናል እነሆ።
ለ) የዐማሮች ጭፍጨፋ በገለምሶ (ሀብሩ ወረዳ፣ ምዕራብ ሐረርጌ )
የገለምሶውን እልቂት ብዙ ሰው አያውቀውም፡፡ የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ)ም መግለጫ አላወጣለትም። በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በዐማሮች ላይ ከተደረጉት ጭፍጨፋዎች ያንን የሚተካከሉት ጥቂት ናቸው። የጭፍጨፋው መርዶ ለብዙ ዘመናት ተዳፍኖ የቆi ቢሆንም ሞረሽ-ወገኔ ባስጠናው ጥናት ይጭፍጨፋውን መጠን እና ስፋት ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ማኅበረሰብ ለማሣወቅ ተችሏል።
ምዕራብ ሐረርጌ ውስጥ በዐማሮች ላይ እጅግ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀል ሲፈጽሙ ከነበሩት ጨፍጫፊ ዘረኞች መካከል ፈጣሪ በወሰደባቸው ፈጣን እርምጃም ቀጥቷቸው አብደውና የጎዳና ላይ ነዋሪ የሆኑም ይገኞባቸዋል። ማየት ማመን ነውና እስቲ ዝቅ ብሎ የቀረቡትን ከዐማራው እልቂት ጋር የተያያዙ ፎቶግራፎችን ከአጫጭር ታሪካቸው ጋር ይመልከቱ።

ይህ በዚህ ፈተግራፍ ላይ ዝቅ ብሎ የሚታየው ግለሰብ ሐረር ውስጥ 20 አማሮችን የፈጀና ኋሃላ ላይ አብዶ ጎዳና ተዳዳሪ የሆነ ነው። ስሙ አንዳርጌ ይባላል። ከጭፍጨፋው በኋላም ኢህአዴግ ታጣቂ አድርጎት ነበር።
ብቻ አይደለም ህግ በነጠፈበት፣ ፍትህ እንደሰማይ በራቀበት የትግሬ-ወያኔዎች የአገዛዝ ዘመን ይህንን ፣ ወንጀል የፈጸሙት አለመጠየቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ የገደሏቸውን ዐማሮች ንብረት ዘርፈውና ወርሰው በደም ገንዘብ እየተንደላቀቁ ይኖራሉ። ለዚህ ማስረጃ የሚከተለቱን ሕንጻዎች አቅርበናል።

እዚህ ፎቶግራፍ ላይ የሚታየው ግለሰብ ስሙ ሦሪ ሲሆን አያሌ አማሮችን የፈጀና ከናካቴውም ባንድ ወቅት የገለምሶ ከተማ ከንቲባ ሆኖ የተሾመ በአማራ ሕዝብ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈለግ ነፍሰ ገዳይ ነው። ከአንድ አመት በፊት ሥልጣን ለቆ አሁን በከተማው ይኖራል። በተጨማሪም አባቷን በግድያ ያጣች አማራ ጥልፎ አግብቶ አስልሟታል። አሁንም አብራው ትኖራለች።

ይህ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የተከራየው ሕንጻ ባለቤትነቱ የአቶ መሐመድ ቡላ ነው። ይህ ግለሰብ ዐማሮችን መቻራ ከተማ (ምዕራብ ሐረርጌ) ውስጥ ሲገድልና ሲዘርፍ የነበረ ነው። ይህንንም ሕንፃ የገነባው ከዐማሮች በዘረፈው ገንዘብ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ሰው የናጠጠ ሀብታም ሲሆን ብዙ መኪኖችም አሉት።
እንደተመለከተው ጨፍጫፊ ነፍሰ-ገዳዮቹ ዐማሮችን በገፍ እና በግፍ ገድለው፣ ሃብታቸውን ሲወርሱ፣ በተቃራኒው ደግሞ በዐማሮች ላይ የደረሰው የሚከተለው ገፅታ አለው።
በሰኔ 1984 ዓ.ም በገለምሶ ከተማ አካባቢ ባሉ ወፊ፣ ዳንሴ፣ አንጫራና ገለምሶ ከተማ ዐማሮችና ክርሰቲያኖች በኦነግ እና ኢህዴድ ታጣቂዎች እየተለቀሙ ተወሰዱ። አብዛኞቹ በሀብሩ ወረዳ ‹ጥርሶ ገደል› እየታረዱ ተጣሉ። በምዕራብ ሐረርጌ የተለያዩ ቦታዎች የነበሩ አማሮች ከግማሽ የሚበልጡት ተጨፍጭፈዋል፡፡ ብዙዎቹ የተገደሉት የአካባቢው ሰዎች ‹ሜንጫ› እያሉ በሚጠሩት የገጀራ አይነት ነው (ምስሉን ከታች በፎቶግራፍ 5 ላይ ይመልከቱ)።

የብዙዎቹ ዐማሮች አንገት የተቆረጠበት ሜንጫ ምስል
ምዕራብ ሐረርጌ ውስጥ ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ የሆናቸው ብዙዎቹ ዐማሮች አባት፣ አጎትና ታላቅ ወንድም የላቸውም፡፡ በጊዜው በነበረው የኦነግ እና ኦህዴድ አሸባሪዎች በዐማሮች ላይ ባደረጉት ጭፍጨፋ ምክንያት ተገድለውባቸዋል። በዐማሮች ላይ የተፈፀመውም አገዳደል በጅምላ እና እጅግ በማሰቃየት ነው፥ ሰውነታቸው እየተቆራረጠ የራሳቸውን ሥጋ እንዲበሉ የተደረጉ ብዙ ናቸው፡፡ የብዙዎቹን ዐማሮች የራስ ቅል ከአንገታቸው ላይ በሜንጫ እየቆረጡ ከሌላው የሰውነታቸው አካል ጋር «ጥርሶ» ወደተባለው ገደል ወርውረውታል። በ1985 ዓ.ም በተደረገው የአስከሬን ለቀማ በ16 ጆንያ የተሞላ የሰው ጭንቅላት ብቻ «ጥርሶ» ከተባለው ገደል ውስጥ ተለቅሟል። ከ«ጥርሶ» ገደል የተሰበሰበው አስከሬን በሙሉ በገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ተቀብሯል።
በገለምሶ ፣ ሀብሩ ወረዳ ብቻ ያለቁ ዐማሮች ቁጥር ከ5,000 (አምስት ሺህ) ይበልጣል። በጠቅላላው በምዕራብ ሐረርጌ ከ10,000 (አስር ሺህ) የማያንሱ ዐማሮች ተጨፍጭፈዋል። በገለምሶ አካባቢ ብዙ ዐማሮች የተገደሉባቸው ቦታዎች (ቀየዎች) ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ቢታንያ (ደረኩ) ቀበሌ፦ ከገለምሶ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። በዚያ በቁጥር ከ30 የሚልቁ ዐማሮች ተገድለዋል። መምህሬ አሰፋ፣ መሠረት ጌታቸው እና ግዛው የተባሉት ከተጨፈጨፉት ዐማሮች መካከል ይገኛሉ።
በዱቤ ቀበሌ በርካታ ዐማሮች አልቀዋል፡፡
ሀርዲም ቀበሌ (በአሁኑ አከላለል በጉባ ቆሪቻ ወረዳ ውስጥ ትገኛለች) ከገለምሶ ከተማ 12 ኪሎ ሜትር ያህል ትርቃለች። በዚህ ቀዬ ያለቁት አማሮች ቁጥራቸው ከ2,000 (ሁለት ሺህ) ይበልጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አንድም ዐማራ የለም፣ ወይም በዐማራነታው አይታወቁም። የቀሩ ዐማሮች ካሉም ኃይማኖታቸውን ወደ እስልምና ካልቀየሩ አሁንም በእድር እንዲጨመሩ አይደረግም። በቀየው የነበረውን የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ (አቡዬ) ቤተ ክርስቲያን የጃራ እና የኦነግ ታጣቂዎች ስላቃጠሉት ታቦቱ ወደ ዳንሴ ተወስዶ በደባልነት አሁንም በዚያ አለ።
በልበልቲ ቀበሌ፣ ከገለምሶ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። በዚህ ቦታም ከ2,000 በላይ ዐማሮች አልቀዋል።፡ አቶ ገብሬ አወቀ የሚባልን ግለሰብ ሕዝብ በተሰበሰበት በሚስማር እንደ ክርስቶስ እጅና እግሩን ቸንክረው በመጀመሪያ ብልቱን ከዚያም የተለያየ የአካል ክፍሉን እየቆራረጡ ለራሱ እያበሉ ገድለውታል።
ዲክቻ ቀበሌ፦ ከገለምሶ ከተማ 12 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። በዚያ ከ50 በላይ ዐማሮች ተገድለዋል።
ወይኒ ጉዶ ቀበሌ፣ ከገለምሶ በ5 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። በዚያ ብዙ ዐማሮች ተገድለዋል።
ወይኒ ቀሎ ቀበሌ ፣ ከገለምሶ 3 ኪሎ ሜትር ያክል ይርቃል። ከ300 በላይ ዐማሮች ተገድለዋል።

ተሰማ ካሣ ይባላል፤ አባቱን መቻራ ከተማ ለስብሰባ ጠርተው በሜንጫ ቆራርጠው የገደሉት (በዚያን ጊዜ ህጻን ነበር) ተሰማ ካሣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኅሊናው ታውኮ የአእምሮ በሽታ ሆኗል። አሁን ብዙ አይናገርም፤ ዝምታን ብቻ ይመርጣል።

ሀቦ፣ልጆቿ ሙሉ በሙሉ የተገደሉባት እናት፤ የአእምሮ ሕመምተኛ ሆና በዚህ መልኩ መቻራ ከተማ ውስጥ ትኖራለች
በጥናቱ ውስጥ የተሳተፉ የአይን አማኞች የሰርክ ተግባራቸውን ሊከውኑ ሲሄዱ በሚገርም ገጠመኝ ባይናቸው በብሌኑ ያዩትንም በዝርዝር ጠቅሰዋል። በጅምላ ያለቁ አማሮችን ጭንቅላት የጫነ ገልባጭ ካልታወቀ ቦታ አምጥተው ገለምሶ አውሳይድ ወንዝ አጠገብ ካለ ጫካ ሲገለብጡ ያዩ አንድ የጥናቱ ተሳታፊ ካህን ጢሻ ውስጥ ተሸሽገው የተመለከቱትን እንዲህ ብለው ገልጸው ነበር።
«አውሳይድ ወንዝ አጠገብ ወደ ወፍቆሎ ጫካ ሲገለብጡት ተደብቄ እመለከት ነበር። ሙሉ ሽበት ያለበት፤ ግራጫ የመሰለ፤ አልፎ አልፎ ሽበት ጣል ያደረገበት፤ ሙሉ ጥቁርና እራሰ በራ የሆኑ ጭንቅላቶች ከመኪናው ላይ ሲገለብጡ በአይኔ አይቻለሁ። በዚህ ሁኔታ ያየሁት ጭንቅላት ከሁለት ጆንያ ይበልጣል።
ሌላው አንድ አባቱን የገደሉበት ሰው ሲናገር እንዲህ አለ« እኔ ቀደም ብዬ የምኖር ድሬደዋ ነው። አባቴ የሚኖረው በበደኖ አውራጃ ፈርዳ ወረዳ ፉርዳ ቀበሌ ነበር። የመንግስት መናወጥ ሲመጣ በ82 አም አባቴን እኔ የምኖርበት ድሬደዋ አመጣሁት። ወዲያው በ83 አም መንግስት ተለወጠ። እናቴ ግን ከዚያው ትኖር ነበር።የቀበሌው አስተዳዳሪ መሐመድ ሃሰን የተባለ ግለሰብ እናቴን ሄዶ «ለምንድነው ባለቤትሽ የማይመጣ አሁን እኮ ሰላም ሆኗል። በሰላም መኖር እየቻለ በእርጅና ለምን አገር ይለቃል? ይላታል። አታሎ አባቴ ያለበትን አድራሻ ከእናቴ ተቀበለ። ድሬደዋ የቀበሌው አስተዳደር መጣና አባቴን ወደ «ሀገሩ» እንዲመለስ ይለምነዋል።አባቴ «እሺ»ብሎት አምኖት ተክትሎት ሄደ።ፉርዳ ሲደርስ ግን ወደ ናፈቃት ሚስቱ አልገባም። ታሰረ።
እህቴን «እንፍታው 20 ሺህ ብር ስጪንና!» አሏት። 20 ሺህ ብር ተበድራ ከፈለች። ግን ብሩንም ወስደው አባታችንንም ወደ ገደል ጨመሩት። ከእርሱ ጋር ገደል የተጨመሩት ሰዎች የአበበ ምትኬ ባለቤት ወ/ሮ አልማዝ፤ ወ/ሮ የሺ፤ዘውዱ ጨፍቅ፤ወርቄ አሸናፊ፤ሙሉጌታ ትርፌ የሚባሉ ይገኞበታል(ከወተር የመጡ ሰዎችም አሉበት)።» ነበር ያለው።
አርሲ አካባቢ የሆነውን እልቂት በተመለከተ አንድ በጥናቱ የተሳተፉ ምስክር እንዲህ ብለው ነበር።«መስከረም 10 ቀን 1984 አም ኦነግ መጣ። ዘሪሁን የሚባል አንድ የአገልግሎት ሠራተኛ፤ ሥራውን የሚያከናውነው በበቅሎ እየተመላለሰ ነበረ። በጥይት መንገድ ላይ ተገደለ።
መስከረም 17 ቀን በጀጁ ወረዳ አቡሌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የአቶ እልፍነህ ጥግነህን 17 የቀንድ ከብቶች ተነድተው ተወሰዱ። በዚሁ እለት መርቲ ጀጁ ወረዳ ደግሞ አቶ እሸቱ ከነልጁ በጥይት ተገደለ። በዚህ ጊዜ የሚደረጉ አነስተኛ ግጭቶች የዐማሮችን ሀብት መቀማት(መውረስ) ነበሩ። ችግሩ አሁንም እየተባባሰ መጣና መስከረም 29 ቀን የአቶ አክሊሉ አበበ ሚስትና ልጅ በጥይት ተመቱ። የአቶ አክሊሉ አበበ ባለቤት ብትተርፍም ልጃቸው ግን ወዲያውኑ ሞተ። ከ6 ቀን በኋላ ጥቅምት 4 ወንጀሉ ቀርሳ ቀበሌ በአንድ ጊዜ 9 ሰዎች በጥይት ተጨፍጭፈዋል። ከተወሰነ ቀን በኋላ ኦህዴድ መጣ። ኦህዴድ በመጣበትም ቀን 2 ሰዎች ተገደሉብን። በወንጀሎ ቀርሳ ቀበሌ አቶ ፈቃዱ አባወሎን ከነባለቤታቸው (ሁለቱም ያረጁ አዛውንቶች ነበሩ) ቤታቸው ተዘግቶ ተቃጠሉ። ዐማራ ጋራ ከሚባል አካባቢ አንድ ሰው ባንካሴ ወግተው ወደ ገደል ወረወሩት። እንዲያውም ከቀናት በኋላ አስከሬኑ ከዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ነው የተገኘው መሬት ሳይነካ። አቶ አበበ የሚባሉ የአካል ጉዳተኛ አዛውንት ነበሩ። ሙሉ አካላቸው ስለማይንቀሳቀስ የሚያነሳቸው የሚጥላቸው ሌላ ሰው ነው። ወደ ቤታቸው ሲገቡ እሳቸውን አገኙ። ከተኙበት አልጋ ላይ በጥይት ገደሏቸው። በርባ ጉጉ ደጋማ አካባቢዎች ግን እልቂቱ ከዚህ በበለጠ እየከፋ ሄደ።……….» በማለት ረዥሙን የግድያ ታሪክ በስፋት ተናግረዋል።
የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት
የኦነግ እና የጃራ ወታደሮች በ1984 ዓ.ም. በተለያዩ ጊዜያት፦
የዳንሴ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን በላውንቸር ጥይት ተኩሰው በመምታት በሙሉ አቃጥለውታል፤
የከተራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን እና የመቃብር ቤቶችን ሁሉ ሲያቃጥሉ፣ የጣራ ቆርቆሮውን ነቃቅለው ወስደዋል፣ የቤተ ክርስቲያን ንብረትም በዝርፊያ አውድመዋል፤
የጀልቦ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንም በተመሳሳይ መልኩ የጣራ ቆርቆሮ ነቃቅለው ወስደዋል፤
በዳንሴ ገበቦ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ቤተ ክርስቲያንን የጣራ ቆርቆሮዎች ነቃቅለው ወስደዋል።
ሐ) የክፍል 2 ማጠቃለያ
ብዙም ብዙም ሆነ። አገር ሰላም ብለው ወገናቸውንም በምንም ሳይጠራጠሩ የሠርክ ሕይወታቸውን ለመምራት ይሯሯጡ የነበሩ ዐማሮች በገዛ አገራቸው እንደ ዱር እንሰሳ እንየታደኑ ተጨፈጨፉ። ስለዚህ በዚህ ሥርአትና ሕግ በሌለበት አገር ምርጫው እራስን ማዳን ነው። ህግማ ቢኖር እነዚህ ወንጀለኞች ዛሬ ሥራቸው የዘረፉትን ሃብት መብላት ሳይሆን ወህኒ መማቀቅ ነበረባቸው። ህግማ ቢኖር ቀድሞውንም እንዲህ ያለ ነገር ባልተፈጸመም ነበር። ህግማ ቢኖር «የዐማሮች የዘር ማጽዳትና ማጥፋት ወንጀል መርማሪ ኮሚሺን» ተቋቁሞ እውነቱ ፍርጥርጥ ብሎ ይወጣ ነበር። ህግ ኖሮ ወንጀለኞች የጥፋታቸውን አግኝተው ቢሆን ኖሮ በያዝነው አመት ሳይቀር በሸዋ ከመዲናችን አዲስ አበባ 60 ኪሊሜትር ርቀት ላይ ዐማሮች ቤታቸው ተቃጥሎ ንብረታቸው ተዘርፎ መድረሻ አያጡም ነበር።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ በጎሰኞች እጅ ሥራ እንደድሬቶ ጨርቅ የተጣጣፈች ፤ ታሪካዊ ሚናዋ የተንኳሰሰ ፤ ከቶ ተሰምቶና ሆኖ የማያውቁ ብጥስጣሽ ባንዲራ ብጤዎች በየመንደሩ የሚውለበለብባት ፤ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ሕዝቦች ሳይሆኑ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ የፈረንጅ ጸሐፍት እንዲሚሉት «የጎሳዎች መጠራቀሚያ» መስላለች። የአለምአቀፍ ሚናዋንና ታሪካዊ ድርሻዋን የተነጠቀች፤ አሃዳዊነቷ የተሸረሸረ፤ ሕዝቧ የጎሪጥ የሚተያይባት፤ የትግሬ- ወያኔ አናሳ መሪዎቿ በቅምጣቸውም ይሁን በእንቅስቃሲያቸው እንዳሻቸው የሚያምሱት ፣ እንቅልፍ የሚነሱት ሕዝብ ያላት ሆናለች። ዛሬ «አለች» የምትባለው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር የራቃት፣ ጦር ሃይሏ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንኳን በወጉ ባላጠናቀቁ ፣ ትምህርት ጠልተውና ሳይቀናቸው ሲቀር ጫካ በገቡ ወንበዴዎች ጀነራል ተብዬዎች የምትመራ ፣ ባለታሪክ የነበረችና አሁን ግን ቀን የጣላት አገር ነች። እንዲህ አይነቱን ተራራ የሚያህል እውነታ የማህበራዊና ታሪካዊ ውድቀት የሚያሳይ የተለየ ማጉሊያ መነጽር የለም። የሚያዩትንና የሚሰሙትን ከማሰላሰል ውጭ።
ሰዎች ማመን ሲሳናቸው ወይም ጭብጡ ከጉጉታቸው እንደሰማይና መሬት ሲራራቅባቸው ቁልጭ ብሎ የወጣውን የገሃዱን አለም ሲክዱት ማየት በእኛ ብቻ አልተጀመረም። እውነታው ግን ወደድነውም ጠላነውም ፣ ፈለግነውም አልፈለግነውም ፣ አገራችን የአናሳዎች መምነስነሻና የብዙሃኑ መጠበሻ ሆናለች። በተለይም ለዐማራው የስቃይ ምድር ሆናለች። ኢትዮጵያዊነት እንደቅንጦት በሚታይበት ዘመን መላው ምንድነው? የአንድነት ሃይሎች የሚባሉት በዙሪያው በሌሉበትና የትም ባልደረሱበት በዚህ ወቅት እነሱንስ በመጠባበቅ ዐማራው እስከመቼ የመስዋእት በግ እንደሆነ ይቀጥል? አማራው እንዲህ በገዛ አገሩ ከመጨፍጨፍ የበለጠ ሊያሰባስበው የሚችል የጋራ ሁነት ምን ሊሆን ይችላል? አማሮች እንደዚህ መከራ ሲጫናቸውና ታላቅ ቀውስ በተጋፈጣቸው በዚህ ዘመን ማንስ ነው የሚደርስላቸው? በዘር መደራጀት አዎ አይረባም! ኋላ ቀርነት ነው። ግና ሰዎች በዘራቸው ተነቅሰው ሲጠቁ ተደራጅተው ቢከላከሉ ዘረኛ የሚያሰኛቸው የትኛው መስፈርት ነው? ዘረኝነት /RACISM/ የሚለውን ቃል በየትኛውም ቋንቋ ብንመረምር አንዱም መመዘኛ ዐማሮች እራሳቸውን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት አይጻረርም፤ በዘረኝነት ጎራ አያስፈርጃቸውም። ህግም እንኳን ቢሆን አልሞት ባይ ተጋዳይነትን ይደግፋል። «በዘር መደራጀት ምን ይጠቅማል?» እያልን «በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት» የምንል ኢትዮጵያውያን ፣ በተለይም ዐማሮች ፣ ታዲያ ይህንን እልቂት እንዴት እናቁመው ትላላችሁ? ለመሆኑ ሰዎች ምን ቢያዩ ይሆን «ይሄስ በቃ!» የሚሉት። ጊዜው ሳይረፍድና ዘረኞች ጭራሹን ሳይበታትኑን እንሰባሰብ።
በስሜት የሚነዱ ወንጀለኞችን በመለማመጥና በማግባባት አደብ ማስገዛት እንዳልተቻለ በታሪክ አይተናል። የሚጋልቡትን የህልም ኮሪቻ ከስራቸው መናድ ግድ ይላል። እጃቸውን ሰብስበው እንዲቀመጡ እዚያም ቤት እሳት እንዳለ ማየት አለባቸው። ለዚህም ሞረሽ-ወገኔን በማጠናከር እህት ወንድሞቻችንን ከኋላ ቀሮች ጭፍጭፋ ይታደጉ። ምናባዊ ወደ መሆን የተቃረበችውን ኢትዮጵያን እንደ ጭምብል በማጥለቅና «ለኢትዮጵያ እንጂ ለአማራነት አይደለም የምቆመው» በሚል የቀን ህልም አማራውን ማዘናጋት ስህተት ነው። አማራው ከተደራጀ ከራሱ አልፎ ለኢትዮጵያ መድህን እንደሚሆን በኢትዮጵያ ምድር የሚኖረው ዜጋ ይቅርና ፈረንጆቹም ሳይቀሩ ጠንቅቀው ያውቁታል። ቢያንስ መሬት ላይ የሚታየውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዳላየ በማየት ለወገኖቻችን መጨፍጨፍ አስተዋጽኦ ከማድረግ ብንታቀብ ይበጃል እንላለን።
የሞተ ሰው ለተፈፀመ ወንጀል አስረጂ ሆኖ አይቀርብም። አስረጂዎች እኛ ተቆርቋሪዎች፣ እኛ በሕይወት ያለን፣ የሰብአዊነት ትርጉሙ የገባን ዜጎች ድርሻ ነው። የዐማራን እልቂት ለማጋለጥና ያላግባብ ለተጨፈጨፉት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ጥብቅና ለመቆም ዐማራ መሆን አይጠበቅም፤ ሰው መሆን ብቻውን በቂ ነው! በሌላ በኩልም ሜዳ ሲቃጠል ተራራ ይስቃል እንዳይሆንም ያሰጋል። ይህ እንዳይሆን ቅዱሱ መጽሐፍ እንደሚለው «ሠይፍ የመዘዙ በሠይፍ እስኪጠፉ» ወይንም ከገቡበት ቅዥት አለም ነቅተው ከገሃዱ አለም ጋር እንዲታረቁ፣ ሞረሽ ለአለቁት ሰማእታት አማሮች በህግና በሰለጠነ መንገድ መፋረድን በመምረጥ ይህንን ጥናት በማስረጃነት ይዟል። ይህንን ወንጀል መፋረድ አግባብ ነው የሚሉዐማሮችም ሆኑ ማናቸውም ኢትዮጵያውያን የሕግ እውቀት ያላቸው በሙያቸው፤ የተቀሩት በገንዘባቸውና በማናቸውም ሊያግዙ ይችላሉ በሚሏቸው መንገዶች ሁሉ እንዲተባበሩ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ጥሪውን ያቀርባል።
ዐማራው ይህንን ታሪካዊ ወቅት ለመራመድና ስብእናውን ለማስከበር የሚዘልቃቸው በሮች፣ የሚያቋርጣቸው ውጣ ውረዶች፣ የሚጋፈጣቸው «ጭራቆች» ቢኖሩትም፣ ፈተናዎቹን ሁሉ በድል እንደሚወጣ ከቶ ላፍታ መጠራጠር አይቻልም።
(የመግለጫውን ክፍል አንድ ይህንን ሊንክ ቢጫኑ ያገኙታል)
ዐማራን ከፈፅሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ፈለገ-አሥራት የትውልዳችን ቃልኪዳን ነው!
 Source: http://www.moreshwegenie.org/