በ‹‹እነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ›› መዝገብ ሥር የሚገኙ ተከሳሾች መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ

0
899

27-11-2015

By Eyoel Fisseha Damte

አቶ ሀብታሙ አያሌውና ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ መከላከያ ምስክር ሆነው ቀርበዋል

ፍ/ቤቱ ቀሪ የመከላከያ ምስክሮችን ለመሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል

በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው በ‹‹እነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ›› መዝገብ ሥር የሚገኙት ተከሳሾች ከሕዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ መከላከያ ምስክሮቻቸውን ማስደመጥ ጀመሩ፡፡

ሰኞ ሕዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ችሎት ከተገኙት ተከሳሾች መሃል 10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ካስመዘገቧቸው 8 መከላከያ ምስክሮች መሃል 7ቱን አስደምጠዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ማክሰኞ ሕዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም መከላከያ ምስክሮችን ማድመጥ የቀጠለ ሲሆን፤ በዕለቱ አቶ ተስፋዬ ያላስደመጡትን ቀሪ የመከላከያ ምስክራቸውን አሰምተዋል፡፡ ከአቶ ተስፋዬ በመቀጠል 6ኛ ተከሳሽ አቶ ዮናታን ወልዴ ካስመዘገቧቸው 5 መከላከያ ምስክሮች መሃል አራቱን አሰምተዋል፡፡ የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቃ የሆኑት አቶ አምሃ መኮንን ለዚህ ዜና ፀሐፊ እንደገለፁት፡- ደምበኛቸው አቶ ዮናታን ወልዴ ሕዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም በተሰየመው ችሎት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 142 መሰረት የመከላከያ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በመከላከያ ቃላቸውም ክሱ አራት ፍሬ ነገሮች እንዳለው በመግለፅ፤ የቀረበባቸው ክስ የሀሰት ውንጀላ መሆኑንና ከቀረበባቸው ክስ መሃል አንዳቸውንም እንዳላደረጓቸው ለፍ/ቤቱ በሰጡት የመከላከያ ቃል መግለፃቸውን ጠበቃቸው አስረድተዋል፡፡ አቶ ዮናታን ወልዴ የቀረበብኝን ክስ ለመከላከል ይረዱኛል በሚል 5 መከላከያ ምስክሮችን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 4ቱን አሰምተዋል፡፡ የተከሳሹ 1ኛ መከላከያ ምስክር የሆኑት አቶ ኃይሉ፣ ከዮናታን ጋር ለ17 ዓመት የቀረበ ጓደኝነት እንዳላቸው ገልፀው፤ አቶ ዮናታን ወሰዱት የተባለው ስልጠና ማህበራዊ ድረገፆችን በተሻለ ለመጠቀም እንደሚያስችል መሆኑንና ከሽብር ድርጊት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልፀዋል፡፡ ስልጠናዎቹን በማስመልከትም ዮናታን ስለስልጠናው ገልፆላቸው እንደነበርና እሳቸውም ስልጠናዎቹን ለመሳተፍ ፍቃደኝነታቸውን በመግለፅ ስልጠናዎቹን ለመሳተፍ “ሲቪያቸውን” ለድርጅቶቹ መላካቸውንና በኋላም ባላወቁት ምክንያት ስልጠናው ሳይሳካ መቅረቱን ለፍ/ቤቱ አስረድቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪነትም 6ኛ ተከሳሽ አቶ ዮናታን ወልዴን ለ17 ዓመታት ጓደኛቸው እንደመሆኑ መጠን በደንብ እንደሚያውቋቸውና የተለየ ነገር ማድረግ ቢፈልጉ እንኳ እሳቸውን ሳያናግር ምንም ነገር እንደማያደርግ ገልፀዋል፡፡ ከአቶ ኃይሉ በመቀጠል ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ለአቶ ዮናታን ወልዴ 2ኛ መከላከያ ምስክር ሆነው በመቅረብ የምስክርነት ቃላቸው ሰጥተዋል፡፡ አቶ አስማማው፣ አቶ ዮናታን ወሰዱት በተባለው ስልጠናን በማስመልከት የተናገሩ ሲሆን፤ የስልጠናዎቹን አላማ እንዲሁም አሰልጣኞቹም እነማን እንደሆኑ፣ ስልጠናዎቹም ሕገወጥ አላማ የሌላቸው መሆኑንና ስልጠናውን የሚሰጡት ድርጅቶችም ተጠያቂነት እንዳለባቸው በዝርዝር ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ረቡዕ ሕዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም ምስክር መስማቱን የቀጠለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ችሎት የዮናታን ወልዴን ቀሪ መከላከያ ምስክሮች መስማቱን ቀጥሏል፡፡ 3ኛ መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው የዓቃቤ ሕግ 3ኛ ምስክር ሆኖ የቀረቡት አቶ ኢዮብ ታደሰ የተባሉት ግለሰብ ‹‹በዮናታን ላይ ለመመስከር የተገደዱት በደረሰባቸው ጫና የተነሳ መሆኑን‹‹ እና ‹‹ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት መሆኑንና ከዮናታን ወልዴ ጋር ትውውቅ እንደሌላቸው›› በሚሉ ጭብጦች ላይ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ በሰጡት የምስክርነት ቃል ላይ በአቶ ዮናታን ወልዴ ላይ የአቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ የቀረቡት፤ አቶ ኢዮብ ታደሰ ‹‹በዮናታን ላይ የምትመሰክር ከሆነ ትፈታለህ›› መባሉን እንደገለፁላቸው ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ፣ አቶ ኢዮብ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ልዩ ቦታው ‹‹ሳይቤሪያ›› ተብሎ በሚጠራው ቦታ እያሉ በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ የተነሳ መራመድ ይቸገሩ እንደነበር ማስተዋላቸውን ገልፀዋል፡፡ በአቶ ዮናታን ላይ የማትመሰክር ከሆነ ከእስር ልትለቀቅ አትችልም እንደተባሉ፣ ባለቤታቸውና ልጃቸው እሳቸው በመታሰራቸው የተነሳ እንደተቸገሩ እንደገለፁላቸውና በዚህ ጫና የተነሳም በአቶ ዮናታን ወልዴ ላይ ለመመስከር እንደተገደዱ ለፍ/ቤቱ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ከአቶ ሀብታሙ በመቀጠል 1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ለአቶ ዮናታን ወልዴ በ4ኛ መከላከያ ምስክርነት በመቅረብ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዮናታን ወልዴ እንዲወስድ የጠቆሙት ስልጠና ምን እንደነበር፣ በማን በኩል ሊሰጥ እንደነበር፣ ስልጠናዎቹ ከሽብርና ከአመፅ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው እንዲሁም ዮናታን ወልዴንና 3ኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክርን አስተዋወቋቸው ተብሎ በክሱ ላይ የተጠቀሰው ከእውነት የራቀ መሆኑን በሚገልፅ ጭብጦች ላይ አቶ ዘላለም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከአቶ ዮናታን ወልዴ 4ኛ መከላከያ ምስክር አቶ ዘላለም በማስከተል 8ኛ ተከሳሽ አቶ ሰለሞን ግርማ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ግርማ ያስመዘገቧቸውን ሶስት መከላከያ ምስክሮች አስደምጠዋል፡፡

የአቶ ዮናታን ወልዴ 5ኛ መከላከያ ምስክር የሆኑት አቶ አብርሃ ደስታ የምስክርነት ቃላቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ፍ/ቤቱ አቶ አብርሃ ደስታ ለሚገኙበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አብርሃ ደስታን እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አብርሃን ሊያቀርብ አልቻለም፡፡ ይህን በማስመልከት የዚህ ዜና ፀሐፊ ጠበቃ አቶ አምሃን አነጋግሮ ነበር፡፡ አቶ አምሃ፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳላወቁና ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በሚገኙና በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ በተመዘገቡ ተከሳሾችን በተመለከተ ፍ/ቤቱ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ሐሙስ ሕዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም በቀጠለው የችሎት ውሎ 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ካስመዘገቧቸው 11 መከላከያ ምስክሮች መሃል 5ቱን አሰምተዋል፡፡ ከሰኞ ሕዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በነበረው የፍ/ቤት ውሎ 9ኛ ተከሳሽ አቶ ባሕሩ ደጉ ብቻ ምንም ምስክር ሳያሰሙ ቀርተዋል፡፡ አቶ ባሕሩ ደጉ፣ 8 መከላከያ ምስክሮችን ማዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለሕዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ዳኞች ባለመሟላታቸው የተነሳ ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሕዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡

ፎቶ፡- ከግራ ወደ ቀኝ ዘላለም ወርቅአገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴና ባሕሩ ደጉZelalem, Yonatan and Bahiru

ፎቶ ፡- ከዘብርሃን ብሎግ የተወሰደ

[Google]