ስለ አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅዐገኘሁ…

0
1060

 

ze4

Zelalem Workagegnehu (glasses) with Habtamu Ayalew

በተድላ ደስታ (PhD)

ነሃሴ 12, 2007

ከስራና ትምህርት መስተጋጎል፣ ቤተሰብን እና አዛወንት ወላጆችን ከእስር ቤት ፍርድ ቤት ማንገላታት፣ ያለተጠበቁ የገንዘብ ወጪዎችን ማውጣት፥ ለጠበቃ፣ ለትራንስፖርት፣ ለምግብ፣ ቤተሰብ: ያለጧሪ ወይም ረዳት መቅረት፣ በተለይ ደሞ በአሸባሪነት መከሰስ፣ ከዛም መታሰር ፣ታስሮም በሰቆቃዎች መቀጣት፣ በእስር ወቅትም በሽታን መሸመት እነዚህ ሁሉ ማናችንም ላይ እንዲከሰቱ የማንፈልጋቸው ግን የተከሰቱ ናቸው።

ዘላለም ወርቃገኘሁ ጋሻው የረጅም ግዜ ጒደኛዬና  ደ ብርሃን ብሎግ ላይ ሲጦምር የቆየ ፅኑ ሰው ነው። በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ሲባል መቼም ሰምታችዃል። ዘላለም ከታሰረና ከላይ  የገለፅኳቸውን መከራዎች መቀበል ከጀመረ ኣሁን አንድ አመት ከአንድ ወር ሆነው። ህዳር ፪፻፯ አገር ቤት በሚታተም  ጋዜጣ ታትሞ የወጣው ክስ እንዲህ ይላል “የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር ፮፭፪፨፪፻፩ን በመጥቀስ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፩፱ኛ ወንጀል ችሎት፣ ጥቅምት ፪፩ ቀን ፪፻፯ ዓ።ም። ከቀኑ ፲፡፴ ሰዓት በኋላ ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ ዘላለም ወርቅነህ (የታይፕ ስሕተት ነው ወርቅዐገኘሁ ለማለት ነው )፣ ዮናታን ወልዴ፣ አብርሃም ሰለሞን፣ ሰለሞን ግርማ፣ ባህሩ ደጉ፣ ተስፋዬ ተፈራ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽና የሸዋስ አሰፋ ናቸው፡፡”

የተጠርጣሪዎቹ የክስ መዝገብ መጠሪያና አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ዘላለም (ወርቅዐገኘሁ) የተባለው ተጠርጣሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪና የግል ሠራተኛ መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል፡፡ ተጠርጣሪው የግንቦት ፯ አመራር ነው ከተባለው ተድላ ደስታ (እኔን ነው) ከሚባለው ግለሰብ ጋር ከ፪፲፻ ዓ።ም። ጀምሮ በስልክና በፌስቡክ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዴት እንደሚመጣ ሲመካከሩ ከርመው፣ በ፪፻፫ ዓ።ም። ግንቦት ወር ላይ የግንቦት ፯ አባል መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡ የሁለቱ ግንኙነት እንዳይታወቅ deresetariku@gmail.com የሚል አድራሻ በመክፈት፣ ግንኙነታቸውን ማጠናከራቸውን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ በ፪፻፬ ዓ።ም። ደግሞ ለግንቦት ፯ አባል የሚሆኑ እየመለመለ እንዲልክና በዓረቡ አገር የተከሰተው ሽብር በኢትዮጵያም ተከስቶ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአመጽ ለመጣል በሴል እንዲያደራጅ፣ ከተድላ ደስታ ጋር መወያየታቸውን ክሱ ያብራራል፤ ዘላለም ወርቅነህ (ወርቅዐገኘሁ) የሚጠቀምበት አሥር ሺሕ ብር ከግንቦት ፯ አመራረ ተልኮለት መቀበሉንም ክሱ ይጠቁማል፡፡  ዘላለም ወርቅነህ deresetariku@gmail.com የሚለው አድራሻና የፌስቡክ አድራሻቸው እንዳይታወቅ Debirhanblogandargachewtsige@facebook.com የሚል ሌላ ማኅበራዊ ድረ ገጽ በመክፈት፣ በአንድ አገር በአመጽና በግጭት ማኅበራዊ ለውጥ የሚመጣበትን ማብራሪያ የሚጠይቅ መልዕክት መላላካቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያን በአመጽ እንዲዘጋ ቢደረግ ውጤት ሊመጣ እንደሚችልም መምከሩን ክሱ ያመለክታል፡፡” ይሄ ብቻ አደለም። የዘላለም ክሶች ሌሎችም ናቸው።  ስለጎንደር ዩንቨርሲቲ ረብሻ በፈረንጆች አቆጣጠር ፳፩፩ መፃፉና ይህም በውጭ አገር ባሉ ድህረ ገፆች ላይ መውጣቱ፣ ሃገር ቤት ውስጥ ካሉ ጓደኞቹ ጋራ ስለፖለቲካ መወያየቱ መምከሩ ሁሉ በክሱ ወስጥ ተጠቅሰዋል።

የተከበሩ ከሳሾች ከፍተኛ የሆነ ስልጣን ለኔም ለዘላለም ወርቃገኘሁም አሽረውናል። ለዛውም አመራር!

ከዘላለም ጋራ ሌሎች ሶስት ጓደኞቹ ታስረዋል: ዮናታን ወልዴ፣ አብርሃም ሰለሞንና ባህሩ ደጉ፣  ጥፋታቸው ደሞ አንድ አሜሪካን አገር ያለ ኢትዮጲያውዊ ጋዜጠኛ አለ ባለው የኢንተርኔት ስልጠና ላይ ለመካፈል በማመልከታቸው። ክሱ ግን የሽብር ስልጠና ነው ይለዋል። ስለዚህ ጉዳይ ወደፊት በሰፊው እናገራለው። ለዐሁኑ ግን ዘላለም ላይ ላተኩር።

የክሱን ትንተና ለናንተ ልተወው ነገር ግን እኔም እሱም የማንኛውም የፖላቲካ ፓርቲ አባል አደለንም። ነገር ግን ለተጎዱ አዝነናል። ላዘኑና ለተከዙ፤ ለተበደሉ ሁሉ ከከንፈር መምጠጥ በላይ እንጥራለን። ስለገዢዎች ሳይሆን ስለተጠቂዎች ብለን ፅፈናል የቻልነውንም ሞክረናል። ይሄ እንግዲህ በዘመነ ሽብር ሐጢያት ነው። በነገራችን ላይ ገዢና ተጠቂ እንደተመልካቹ ነው። እኛ ራሳችንን እንደተበዳዮች ስናይ አሳሪዎቻችን ደግሞ ራሳቸውን እንደ ተባዳይ ያዩ ይሆናል።

አንድ እማልክደው አቋም ግን ኢትዮጲያ ውስጥ መልካም አስተዳደር መስፈን እንዳለበት በተለይ ደሞ የብሄሮች የበታችነትና የበላይነት (ethnic hegemony) አብቅቶ የብሄር እኩልነት (ethnic equality) መስፈን ለዐሁኗ ኢትዮጲያ ችግሮች መፍትሄ ነው ብዬ አምናለሁ ለዚህም እስከመጨረሻው የምችለውን ሁሉ አደርጋለው። ይሄም ሽብር ይሆን?

ዘላለም በሰላሳዎቹ የመጀመሪያ እድሜ ክልል የሚገኘ ወጣት ነው። በትምህርቱ በጣም ጎበዝ ከሚባሉት ወስጥ ሊምደብ ይችላል። የመጀመሪያ ዲግሪውን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት ጨርሶ ወደ ቤተሰቦቹ ቤት አዲስ አበባ ከተመለሰ በሁዋላ የተላያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ የግሉን ንግድ ሲሰራ ነበር። ለምሳሌ መቂ አካባቢ እርሻ ጀምሮ ነበር። የተወሰኑት ቢዝነሶቹ ሲቀጥሉ ሌሎቹ ደግሞ ቆመዋል። ከብዙ አመታት እረፍት በሁዋላ ደግሞ ወደ ትምህርት በመመለስ የማስትርስ ዲግሪ ትምህርቱን በ፪፻፮ አም ጀምሮ ነበር። በታሰረበትም ወቅት የመመረቂያ ርእሱን መርጦ ጨርሶ መፃፍ ብቻ ነበር የቀረው። አሁን ቂሊንጦ ወስጥ ምርጥ የመመረቂያ ፅሁፍ ርእሶች እንዳገኘ አምናለሁ።   ትምህርቱን ሲጀምር ብዙ ግዜውን ከፌስቡክ ርቆ ላይብረሪ ያሳልፍ ስለነበር እኔም በግል ህይወቴ በተፈጠሩ ለውጦች ምክንያት ግንኙነታችን ቀንሶ ነበር። አልፎ አልፎ ግን እንነጋገር ነበር።

ስለዘላለም በሃሪ አብረውት ታስረው በቅርብ የተፈቱ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች እንዲሁም እስርቤት ለጉብኝት ሲሄዱ የተዋወቁት ሰዎች ሁሉም “በጣም ትሁትና ጨዋ” ብለው ይገልፁታል። ዘላለም በጣም ጥሩ በሆነ ቤተሰብና ሰፈር ውስጥ ታንፆ ያደገ ልጅ ነው። ሀገሩን የሚወድ ፤ በተለያዩ የምእራብ ሃገሮች ወንድምና እህቶች ቢኖሩትም ፈረንጅ ሃገር ሄዶ ለመኖር የማይጓጓ፤ በሃገሩ ሰርቶ መለወጥን የሚሻ; ብልጭልጭ የማይደንቀው   ሰው ነው።

እንደ ዘላላም ያሉ ምሁሮች የትኛውም መንግስት ቢሆን ለሃገሪቱ እድገት ሲል እስር ቤት ውስጥ ሳይሆን የሃሳብ ማፍለቂያና ማንሸራሸሪያ መዐከል ከፍቶ ሊጠቀምባቸው የሚጋባ ዜጎች ናቸው። ይህን የምለው ዘላለምን እንደግላሰብና እንደ አንድ ብዙ ግዜ አብሮት እንደተወያየ ሰው ሆኜ ነው። በደ ብርሃን ብሎግ ላይ እምፅፋቸው  ትንታኔዎች ብዙዎቹ ከዘላላም የፈለቁ የሃሳብ ውልዶች ናቸው። ከግጭት አፈታት ዘዴዎች መሃል አንዱ አንዱን የሚረታበት ዊንሉዝ (win-lose) ሲስተም ሲባል ሁለቱም ወገኖች የሚያሸንፉበት ዊንዊን(win-win) ይባለል ሶስትተኛው ደሞ ክሪኤቲቪቲ (creativity) ወይም ደሞ አዲስ ያልታሰበ አማራጭ ማመንጨት ነው። ይሄ ቀላል አደለም። የዘላለምን የክሪኤቲቪቲ ችሎታ ለማሳየት የሚከተለውን ምሳሌ ልጥቀስ። ከጥቂት አመታት በፊት የአባይ ግድብ ጉዳይ በግብፅና በኢትዮጲያ የከረረ አለመግባባት በፈጠረበት ወቅት ፤ እኛም ስለዚህ ጉዳይ ለምን አንፅፍም ብለን ሃሳብ በፌስቡክ መላዋወጥ ጀመርን። ዘላለም እንዲህ አለኝ። ግብፅ ዛፍ መትከል አለባት። ለዛፍ ተከላውም ማገዝ አለብን። ሃሳቡ እንዲህ ነው ኢትዮጲያ በዐባይ የመጠቀም ሙሉ መብት አላት፤ ግብፃውያንም በውሃ ጥም እንዳያልቁ የሰብዐዊ ግዴታ አለብን ስለዚህ ሁሉንም የማይጎዳ መፍትሄ ያስፈልጋል። ግብፅ አብዝታ ዛፍ ብትተክል ለዚህም ብትረዳ በቂ ዝናብና ውሃ ይኖራታል። ይሄ ታድያ ሰፋ ብሎ ቢጠና ምርጥ የፖሊሲ አማራጭ አደለም? እንዲህ አይነት ኢትዮጲያውያንን መንከባከብ አይስፈልግም?

ዘላለምን ለማስፈታት

ዘላለምን ለማስፈታት አንድ አመት ሙሉ ዲፕሎማቶች፤ ሸምጋዮችንና እነሱን ሊቀርቡ ይችላሉ የተባሉ አካላትን ሁሉ ተማፀንን: ጠየቅን። የሁሉንም ወገኖች ሃሳቦች የምናስተናግድ መሆናችንን ለማሳየት ሞከርን። ይሄን ሁሉ የዝምታ ዲፕሎማሲ (quiet diplomacy) ስናካሂድ ልንከላከለው የሞከርነው ነገር ሁሉ ለካ ተከስቷል (the damage was done) መከሰትም ብቻ አደለም ኖረነዋል። ሊያደርሱብን የሚችሉትን ሁሉ አድርሰዋል: የክሶችም ክስ የሆነው የሽብርተኘነት ክሱም (slander) ቀጥሏል ።

የሽብርተኘነት ክስ ሲነሳ ሁልጊዜ የሚገርመኘ ነገር አለ። ክፉው የደርግ ስርዐት ፖለቲካንና ጋዜጠኘነትን ሞት የሚል ትርጉም እንዲኖራቸው: አይነኬ አይጠጌ አድርጎ አልፏል። አሁን ደሞ ፖለቲካና ጋዜጠኘነት ሽብር ማለት ሆነዋል። የኢትዮጲያ ጸረ ሽብር ህግ ከአሜሪካንና ከእንግሊዝ የጸረ ሽብር ህጎች ሙሉ በሙሉ የተወሰደ ነው ብለው የዐገሪቱ መሪዎች በብዛት ይከራከራሉ። መቶ ፐርሰንት ኩረጃ! ምንም እንኳን አሽባሪነት በግልፅ የሚያሰጋን ችግርና ሕግም አሥፈላጊ ቢሆንም አሁን ባለው መልኩ ግን መሆን የለበትም እላለሁ። በመጀመሪያ ችግሩ የሚመነጨው በቀልን ያማከለ ህግ አወጣጥ መኖሩ ነው። እሱ ብቻ አደለም አይምሮውን ተጠቅሞ ነባራዊ ሁኔታዎችንና ችግሮቹን አጥንቶ ተገቢ የሆነ ህግ እሚያወጣ ታላቅ መሪ  እና ሲስተም አለመኖሩ ነው። ታላቅ መሪ የራሱን ወገን በፖለቲካዊ ልዩነቶች ብቻ አሽባሪ ብሎ አይፈርጅም፣ አይከስም። ታላቅ መሪ በጥናት እና ምርምር ላይ የተመሰረተ ሽብርን የሚከላከል (ግዴታ ጸረ ሽብር ህግ መባል የለበትም) ህግ ይቀርፃል። ይኸው በዚህ መቶ ፐርሰንት ኩረጃ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል ቀሪው ህዝብ ደሞ ፈርቷል።

ከዐመት በፊት ዘላለም ሲታሰር ሊያስሩት የመጡት ፖሊሶች በጥቆማ ነው የመጣነው ማለታቸውን ሰምቻለው። ከዐንድ አመት በላይም በጠቋሚዎቹ መረጃ መሰረት ዘላለምና ጓደኞቹ ታስረው አካላዊና አእሮአዊ ጥቃቶችን አስተናግደው ተከሰው ፍርድ እየተጠባበቁ ነው። እዚህጋ ነው እንግዲህ የዐሳሪዎቹም የከሳሾቹም የስሌት ስሕተት እሚታየው። አጥፍተውም ቢሆን እንኳን በምክርና ማስጠንቂያ ሊታለፉ የሚችሉ ልጆችን ወደ ቂሊንጦ ሲልኩ የጠቆሙትን ደሞ ወደ ቪላ ቤት ልከዋል። ህሊናው የታሰረው ግን የቱ ነው? የቪላው ወይስ የቂሊንጦው? እነዚህን  ልጆች ቂሊንጦ በመላክና እዛው በማክረም ህጋዊም ፖለቲካዊም ትርፍ ይገኛልን? ይህን እንግዲህ በጊዜ እናየዋለን። ለኔ ግን የተሳሳተ ስሌት ነው።

የነዚህ ግለሰቦች ብዙ መከራከሪያዎቻቸው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርገው፤ ከአንድ አመት በላይ ከሆነ እስር በሁዋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በነፃ ይሰናበቱ ወይንም ይከራከሩ የሚለውን ለመወሰን ለብይን ለሃሙስ ነሀሴ 14/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ማን እንደሆነ ባላስታውስም ይህን የዐንድ አውሮፓዊ አባባልን ልጥቀስ “ክፋትን፤ ውሽትን፤ ጭቆናን ከመጥላትና እነሱንም ለመቀየር የቆሙ ጣእማቸው፤ ኩራታቸውና ጥንካሬያቸው በመከራ ውስጥም አይክዳቸውም፤ አካላቸው ቢሞት እንኳን ይኖራል። ህይወት ከሞት ወስጥ ይመነጫል። ከመስዋእትነት። ከጀግኖች መቃብር ደግሞ ነፍስ ያላቸው ሃገራት ይወለዳሉ::” የኢትዮጲያና የኢትዮጲያውያን ችግር እንዲህ ተቆጥሮ እሚያልቅ አደላም፤ ከሃገር ቤት እስከውጭ አገሮች። ብዙዎቹ ችግሮች ሃገሪቱን በእርቅና በፍቅር ዳግም በማዋለድ ሊፈቱ ይችላሉ፤ ሌሎቹ ደሞ በሌሎች መንገዶች።

እነዘላለም ከዐመት በላይ ያለፍርድ እስር ቤት ናቸው። በፍርሃትም በግል ህይወት ምክንያት የሚጠይቋቸውም አብረዋቸው የሚቆሙት ሰዎች ቁጥር ሊቀንስ ይችላል። እኔ ግን ዛሬም እንደ ትላንቱ እስከመጨረሻው ከዘላለም ጎን እቆማለሁ!

 [Google] 

 [Google]