ዘላለም ወርቃገኘሁ ማን ነው?

0
491

በላይ ማናዬ

09/07/2015

ከዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች የእስር ዜና ትንሽ ዘግይቶ ልክ የዛሬ አመት ሐምሌ 1/2006 ዓ.ም ነበር በአደባባይ ስማቸው ጎልቶ የወጡት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሽና ‹‹የሰሜኑ ፈርጥ›› አብርሃ ደስታ መታሰራቸው በሰዓታት ልዩነት ይፋ የሆነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በታሰሩበት ወቅት ግን ሌላ ማን አብሯቸው እንደታሰረ ማናችንም ቢሆን ለሚዲያ በበቃ ዜና የሰማነው ነገር አልነበረም፡፡ በቀናት ጊዜያት ውስጥ የፓርቲ አመራሮቹ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ስለመታሰራቸው በሰማንበት ጊዜ እንኳ አብረው የታሰሩ ሰዎች ስለመኖራቸው አላወቅንም ነበር፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በእስር ከነበሩበት ማዕከላዊ ምርመራ ወደ አራዳ ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ በቦታው ተገኝቶ የታሰሩትን የፓርቲ አመራሮች ለማየትና አጋርነት ለማሳየት ብዙ ሰው ይገኝ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ግን አንድ ቀጭን ወጣት ከፓርቲ አመራሮች ቀድሞ በፌደራል ፖሊሶች ታጅቦ ወደ ፍርድ ቤት ይመጣ ነበር፡፡ የልጁን ማንነትና የተያዘበትን ምክንያት ለማወቅ ቤተሰቦቹ ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውንና በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ያገኘኋቸውን ሰዎች መጠየቄ አልቀረም፡፡ ዳሩ ግን ቤተሰቦቹም ሆነ ጓደኞቹ ስለዚህ ቀጭን ወጣት መናገር አልፈለጉም፡፡ ፎቶውን ቢሰጡኝና መረጃ ማግኘት ብችል ለሚዲያ ላበቃው እንደምፈልግ ብገልጽላቸውም ልንግባባ አልቻልንም፡፡ ለካ ቤተሰቦቹ ዝምታን የመረጡት የወጣቱ አቋም ‹‹ወደ አደባባይ›› መውጣትን ካለመፈለጉ የመነጨ ኖሯል፡፡
ወጣቱና የፓርቲ አመራሮቹ አራት ወራት የምርመራ ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ከማዕከላዊ ሲወጡና በይፋ ክስ ሲመሰረትባቸው የዚህ ቀጭን ወጣት ስም ከሁሉም ቀድሞ ተገኘ፤ አዎ በዚህ ወጣት ስም በተከፈተ መዝገብ አስር ሰዎች የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው…በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ፡፡ አሁን ቤተሰቦቹም ሆነ ወጣቱ ራሱን መደበቅ አላስፈለገውም-አይችልምም፡፡ እናም ሚዲያዎች የፓርቲ አመራሮችን ጉዳይ ሲከታተሉ ‹‹በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ…›› እያሉ ስሙን ወዳልፈለገው አደባባይ አወጡት፡፡

ዘላለም ወርቃገኘሁ ማን ነው?

በአፍሪካ ውስጥ የፖለቲካ ህይወትን በእስር መጀመር፣ መጨረስ፣ አሊያም ደግሞ እንደ አቅም ግንባታ ስልጣና መሐል ላይ በሰቆቃ የተሞሉትን እና ኢ-ሰብዓዊ የሆነ የምርመራ መንገድ የሚከተሉትን የአምባገነኖች ደህንነት ሰራተኞችን በትር ቀምሶ መውጣት የተለመደ ነው፡፡ ዘላለም ወርቃገኘሁ ግን በፍጹም በዚህ መልኩ በፖለቲከኝነት አደባባይ እወጣለሁ ብሎ አላሰበም ነበር፡፡ ለመሆኑ ‹‹ዘላለም ወርቃገኘሁ ማን ነው? እንዴት እንደ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ ያሉ እውቅ የፖለቲካ ስብዕናዎች (personalities) ባሉበት መዝገብ ሊከሰት ቻለ?››
የተወለደው አዲስ አበባ፣ አዲሱ ገበያ አካባቢ ነው፡፡ ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ (11 ልጆች ያሉበት ቤት) የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ አባቱ አርቲስት (አሁን በህይወት የለም) ነበር፤ እናቱ ደግሞ ጡረታ የወጣች የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡ ዘላለም መካከለኛ ገቢ ያለውና ከፍተኛ የልጆች ነጻነት ባለበት አስተዳደግ ማለፉን ይናገራል፡፡ እንዲያውም አባቱ የአገዛዙ የ‹ዴሞክራሲ› ዲስኩር ሲያሰለቸው ‹‹እኔ ቤት ዴሞክራሲ ከቃሉ በፊት ተግባሩ ነው የገባው›› ይል እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ዘላለም ትምህርቱን የተከታተለባቸው ት/ቤቶች መጠሪያ በራሱ አሁን ላለው የኢትዮጵያዊነት ስሜት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሳያደርጉ አልቀሩም፡፡ አንደኛ ደረጃን ‹‹ኢትዮጵያ ዕድገት››፣ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃን (7ኛ እና 8ኛ ክፍል) ‹‹አርበኞች››፣ እና ሁለተኛ ደረጃን ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› ት/ቤቶች ተከታትሏል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አጠናቅቋል፡፡ የዛሬ አንድ አመት በስርዓቱ የደህንነት ኃይሎች በተያዘበት ጊዜም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደር ት/ት ክፍል በፐብሊክ ፖሊሲ አናሊስስ (Public Policy Analysis) የማስተርስ ዲግሪውን ለመጨረስ የቀረው የመመረቂያ ጽሑፍ ማዘጋጀት ብቻ ነበር፡፡

የዘላለም የእምቢተኝነት መሰረት

ቤተሰብ ነጻ አስተሳሰብን የሚያራምድ እና መብቴን አላስረግጥም የሚል ትውልድ ለመፍጠር መሰረት ነው፡፡ በእርግጥ የአካባቢና የቤተሰብ አስተዋጽኦም ከቤተሰብ የተናነሰ አይደለም፡፡ ዘላለም የፖለቲካ አስተሳሰቡ በአስተዳደጉ የተቀረጸ እንደሆነ ያምናል፡፡ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ አሁን ላይ በማያስታውሰው ምክንያት የእንግሊዝኛ መምህራቸው በመደዳ የክፍሉን ተማሪዎች መቅጣት ትጀምራለች፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ተማሪዎች እንደገረፈች ዘላለም ከመቀመጫው ተነስቶ በተከፈተው በር ሩጦ በመውጣት ወደ ርዕሰ መምህሩ ቢሮ ያመራል፡፡ ራሱን ከድብደባው ካተረፈ በኋላ የሆነውን ሁሉ ለርዕሰ መምህሩ አስረዳው፡፡ ርዕሰ መምህሩ ይዞት ወደ መማሪያ ክፍሉ ሲመለሱ የጅምላ ቅጣቱ እየተካሄደ ደረሱ፡፡ ብዙዎች ተማሪዎች ያለቅሳሉ፡፡ አንዳንዶቹ በተለየ ሁኔታ እጃቸው ሰንበር በሰንበር ሆኗል፡፡ ርዕሰ መምህሩ በጣም ተናዶ እንግሊዝኛ መምህራቸው ላይ ጮኸባት፡፡ በዚህም እሷን ከክፍል አስወጥቶ ተማሪዎቹን አረጋጋ፡፡ ዘላለምም በእቢተኝነት ውጤት አሳየ፡፡ ‹‹ያኔ የሚደግፈኝ ስላገኘሁ የልጅነት ልቤ ኩራት ተሰማት፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ያቺ የመጀመሪያዋ እምቢተኝነቴ በርዕሰ መምህሩ ድጋፍ ባታገኝ ኖሮ አሁን ያለኝን ጭቆናን የማይቀበል ባህሪ አላገኘውም ነበር›› ይላል ዘላለም፡፡
ይህ ሦስተኛ ክፍል ላይ መብትን ባለማስረገጥ የተጀመረው እምቢተኝነቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ የተሸጋገረው በ1991 (የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት) የተማሪዎች ም/ቤት ፀሐፊ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞችን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር፡፡ የኮሚቴው ዓላማ ለጦርነቱ ገቢ ማሰባሰብና የደም ልገሳን ማስተባበር ነበር፡፡ ዘላለም ኮሚቴው ውስጥ የገባው ተማሪውን በመወከል ቢሆንም ያለኮሚቴው እውቅና የት/ቤቱ አስተዳደር ማህተም ያረፈበት ደብዳቤ ቦርድ ላይ በመለጠፍ ‹‹የወታደሮች ምልመላ›› ያደርግ ጀመር፡፡ ዘላለም ይህንን በመቃወም በመጀመሪያ የተማሪዎች ም/ቤት አስፈጻሚዎችን በተቃውሞ አሳመጸ፡፡ በመቀጠልም የትምህርት ቤቱ አስተዳደር የኮሚቴውን ሰብሰባ እንዲመራ፣ አለበለዚያ በተማሪዎች ም/ቤት ማህተም ምልመላውን የሚቃወም ማስታወቂያ የመጻፍ ግዴታ እንዳለበት አሳሰበ፡፡
በጊዜው የኮሚቴው ስብሰባ ቢጠራም ሙግቱ ቀላል አልነበረም፡፡ እንዲያውም ‹‹በጦርነቱ ወቅት ሁሉም ወገን መተባበር አለበት›› የሚል መከራከሪያ ተነሳ፡፡ ያን ጊዜ ዘላለም ‹‹እንደዚያ ከሆነማ፣ ሁሉም ወገን እንደጦርነቱ አካል የሚቆጠር ከሆነ፣ የሻዕቢያ መንግስት አይደር ት/ቤትን በአየር መደብደቡ ተገቢ ነበር›› የሚል መቃወሚያ አስነሳ፡፡ ይህኔ አንድ መምህር ዘላለም አባባሏን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማትን ቃል በመናገር ሀሳቡን ደገፉ፣ ‹‹ይሄ ልጅ እኮ grain of truth አለው›› አሉ፡፡ በመጨረሻም ደጋፊዎቹ በርክተው በት/ቤታቸው የወታደር ምልመላ ማስታወቂያው ተነሳ፡፡ በተመሳሳይ በ1993 ይሄ የዘላለም ወርቃገኘሁ መብትን አለማስረገጥ፣ ለተወከሉለት አካል መቆም አድጎ ለሌሎች አጋርነትን ወደማሳየት ተሸጋገረ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመብት ጥያቄ ባነሱበት ጊዜ እነ ዘላለምም (የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች) ጥያቄያቸውን በመደገፍ ተቃውሞ በወጡበት ወቅት ግንባር ቀደም ተሰላፊ ከነበሩት ተማሪዎች ዘላለም ተጠቃሽ መሆኑ ነው፡፡
ዘላለም ከስርዓቱ አስፈሪ ገጽታ ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጠው ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ አመት ተማሪ በነበረበት ወቅት (ህዳር 1997 ዓ.ም) ነበር፡፡ በወቅቱ በግቢው የውሃ እጥረት ተከስቶ ተማሪዎች ከታንከር በጀሪካን ተሰልፈው እየቀዱ ነበር የሚጠቀሙት፡፡ ይህ ችግር ሳይፈታ ብዙ አዳዲስ ተማሪዎች ግቢው ውስጥ መድረስ ሲጀምሩ በሁኔታው የተበሳጨው ነባር ተማሪ በተቃውሞ ቀስ በቀስ ግቢውን አናወጠው፡፡ ወዲያውም ግቢው በመከላከያ ሰራዊት አባላት ተከበበ፡፡ በወቅቱ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት የአሁኑ ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተሰብስቦ ችግሩን የሚያስረዳ ተወካይ እንዲመረጥ ተጠይቀው ዘላለም ወርቃገኘሁ ከ10ሩ ተወካዮች አንዱ በመሆን ተመረጠ፡፡ ተመራጮች በግቢው እየተዘዋወሩ የተማሪዎቹን ጥያቄዎች ሲሰበስቡ ከዘላለም እግር ስር የማይጠፋ አንድ ሰው ነበር፡፡ ዘላለም ይህን ሰው፣ ‹‹ማነህ›› ሲል ጠየቀው፡፡ ‹‹ፍሬሽ ተማሪ ነኝ›› አለው ሰውየው፡፡ ይሄኔ ዘላለም ‹‹እስኪ የተመዘገብክበትን ስሊፕ አሳየኝ›› ሲለው ሰውየው ሽጉጥ መዝዞ ተማሪ እንዳይጠጋው እያስፈራራ ከግቢ ወጥቶ ሄደ፡፡
ከዚያ በኋላ የተማሪ ተወካዮቹ ነገሩ አላምር አላቸው፤ የኮሚቴው አባላት ከግቢ ሲወጡ ሁለት፣ ሁለት ፖሊሶች ይከተሏቸው ጀመር፡፡ ተወካዮቹም ተመልሰው ግቢያቸው ውስጥ ተሸሸጉ፡፡ ሆኖም ት/ት ማቆም አድማ ተጀምሮ ስለነበር ‹‹የማትማሩ ከሆነ ግቢውን ለቅቃችሁ ውጡ›› ተባሉ፡፡ ይሄኔ ዘላለም ከሌላ አንድ ተመራጭ ጋር ሆኖ በጓሮ በኩል ወደ አዘዞ ሸሸ፡፡ በዕለቱ በፊት በር ከወጡት ውስጥ 8 የተማሪዎቹ ተወካዮችን ጨምሮ 41 ተማሪዎች ታሰሩ፡፡ የተባረረው ተማሪም ማረፊያ እንኳ እንዳያገኝ ካድሬዎቹ ‹‹ለጎንደር አንድ ዩኒቨርሲቲ ቢገነባ እሱንም ሊያፈርሱት ነው›› እያሉ ስማቸውን አጠፉት፡፡ በመጨረሻ ‹‹የታሰሩት ይፈቱ!›› በሚል መደራደሪያ ብቻ የታሰሩት ተፈትተው ተቃውሞው አበቃ፤ ወደ ትምህርት ገበታውም ከእነ ችግሩ ተመለሱ፡፡ ያን ጊዜ ነበር ዘላለም ወርቃገኘሁ የመብት ጥያቄ የሚፋጅ እሳት እንደሆነ የተግባር ትምህርት ያገኘው፡፡ ‹‹ያን ጊዜ ነው የመደበቅ አስፈላጊነትን የተረዳሁት ማለት እችላለሁ፡፡ አደባባይ ሳትወጣ ራስህን ማጎልበት…የአቅምህን መስራት›› ይላል ዘላለም አሁን ከሚገኝበት ቂሊንጦ እስር ቤት ሆኖ፡፡

እስር አደባባይ ያስወጣው ዘላለም

ዘላለም ይህ በእንዲህ ካለፈ እና አዲስ አበባን የሰጥለጥ ፖለቲካ ዝማሜ ከመታት በኋላ (1998) ነበር ትምህርቱን ጨርሶ አዲስ አበባ የተመለሰው፡፡ ምንም እንኳን ንቁ የሲቪል ተሳትፎው ባይቀንስም፣ የአደባባይ ፖለቲከኛ ከመሆን በፊት በቂ እውቀት ማካበት ያስፈልጋል ባይ ነበር ዘላለም፡፡ ‹‹አለበለዚያ ግን የተለመደው የአላዋቂነት ፖለቲካ ውስጥ እዘፈቃለሁ የሚል ስጋት ነበረኝ፡፡›› ስለሆነም ዘላለም መጀመሪያ ችግሩን መረዳትና መፍትሄውን መለየት በሚለው ፈሊጥ ከተለያዩ ሰዎች ጋር እየተገናኘ መነጋገር፣ ማንበብና ወቅታዊ ጉዳዮችን መተንተን እንዲሁም ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎችን መካፈል ማዘውተር አስቀደመ፡፡
በዘላለም እምነት ግንዛቤ መጨበጥ፣ መደራጀትና ወደ ተግባር መግባት በቅደም ተከተል የሚመጡ ነገሮች በመሆናቸው ራሱን በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ገና ማቆናጠጡ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ዘላለም በመጀመሪያው ደረጃ ላይ የእስር ሰለባ ከመሆን አልተረፈም፡፡ ‹‹ምናልባት ያልተረዳሁት ነገር ቢኖር መንግስታችን ንቁ የሲቪል ተሳትፎ ላይ የደረሰ ሰው እንኳን መታገስ የማይችል ደረጃ ላይ መድረሱን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስለኛል ወደ ማዕከላዊ ግዞት ከዚያም ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በሽብርተኝነት ክስ ስም የወረወረኝ፡፡ ከዚያ በፊት በስም ብቻ ከማውቃቸው ፖለቲከኞች ጋር ያውም በአንደኛ ተከሳሽነት፣ በአንድ መዝገብ የከሰሰኝ፣ እንደሚመስለኝ ‹እውቅ ሰዎችን እየሰበሰብኩ ይበልጥ እውቅ አላደርግም› ከሚለው ፍልስፍናው ተነስቶ ሊሆን ቢችልም፣ እኔን ግን አልጎዳኝም፡፡ ከእነዚህ እና ከሌሎችም ሰዎች ብዙ ልምድና ትምህርት ቀስሜያለሁ፡፡ ማን ያውቃል? እኔ ስዘገይ መንግስት ሳያውቀው ወደ አደባባይ መውጫህ ጊዜው አሁን ነው እያለኝ ይሆናል!›› ይላል ዘላለም፡፡ በዚህ ሁኔታም ዘላለም ከ‹‹አደባባይ አልወጣም›› አቋሙ ሊፋታ ቻለ፡፡

ከቋንጃ ቆረጣ ወደ ቁርጭምጭሚት ቅጥቀጣ

ዘላለም ወርቃገኘሁ የዛሬ አመት ለእስር ተዳርጎ ማዕከላዊ ከገባ ጀምሮ ብዙ አሰቃቂ የምርመራ ሂደትን አልፏል፡፡ ዳሩ ግን ዘላለም ‹‹በሌላው ወገኔ ላይ የደረሰ ተመሳሳይ አሰቃቂ ድርጊት ነው የተፈጸመብኝ›› በማለት ላለማስታወስ ይሞክራል፡፡ ይልቁንስ ዘላለም ማዕከላዊ እያለ ያየውን ለየት ያለ ድርጊት ሊነግረን ይፈልጋል፡፡ ይኸውም ‹‹የቁርጭምጭሚት ቅጥቀጣ›› ነው፡፡
‹‹ድሮ በመኳንቱ ጊዜ አሽከሮቻቸው እንዳይኮበልሉባቸው ቋንጃቸውን ይቆርጡባቸው ነበር አሉ፡፡ አሁን ይሄ ተቀይሯል፡፡ እኔ ማዕከላዊ በነበርኩበት ጊዜ በፌደራል ፖሊሶች፣ በሁሉም ክልሎች በሚባል መልኩ የተፈጠረ አሰራር አለ፡፡ ይኸውም በቁጥጥር ስር ያዋሏቸውን እስረኞች እንዳይጠፉ ቁርጭሚትሚታቸውን መቀጥቀጥ ነው፡፡ እኔ ማዕከላዊ በነበርኩበት ጊዜ ብቻ አብዱልፈታህ የተባለ ሰው ከቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ሁሴን ሰዒድ ከወሎ፣ እና ተወኪል ግርማይ ከወለጋ ቁርጭምጭሚታቸው ተቀጥቅጦ መጥተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የካቴናን ችግር ለመቅረፍ የተዘየደ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ በተራ በተራ ከእየአካባቢው እየተለቀሙ የሚመጡ እስረኞች ዓይነት ነው፡፡ እኛ ስንገባ የኦሮሞ ተማሪዎች ይበዙ ነበር፡፡ ኋላ ላይ የጎንደር ሰዎች ተለቃቅመው መጥተው አጥለቀለቁት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ከሶማሌ ክልል የመጡ ተጠርጣሪዎች በዙ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ይደርሳል›› ይለናል ወጣቱ የሽብር ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ፡፡

‹‹ወደፊት!››

ዘላለም ወርቃገኘሁ ዛሬ ላይ ለእስር ከመዳረጉ በፊት ለአደባባይ ያልወጡ ራስንና ሌሎችን በእውቀት የማጎልበት እንቅስቃሴዎችን ሰርቷል፡፡ መጽሐፍትንና ጋዜጦችን አንብቦ ለሌሎችም አስነብቧል፡፡ ከአንድ ጋዜጠኛ ወዳጁ ጋር በመሆንም በጋራ ኢንተርኔት ላይ ይጦምር ነበር፣ እስከታሰረበት ጊዜ ድረስ፡፡ ዘላለምን ለእስር የዳረገው ዋናው ምክንያት እምቢባይነቱ ነው፡፡ ዳሩ ግን ስለተከሰሰበት ጉዳይ በዝርዝር ለመናገር ጊዜው አሁን አይደለም፣ ‹‹ፍርድ ቤት›› የያዘው ጉዳይ ስለሆነ፡፡ ዘላለም በተከሰሰበት ጉዳይ ላይ ለፍርድ ቤት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲሰጥ እንዲህ ብሎ ነበር፤ ‹‹በአቃቤ ህግ እና በፖሊስ ተቀነባብሮ የቀረበብኝን ክስ በተመለከተ ለክሱ እውቅና ላለመስጠት ምንም አልልም፡፡ በክሱ ላይ አስተያየት በመስጠት ለጸረ-ሽብር አዋጁ እውቅና መስጠት አልፈልግም፡፡››
አሁን ዘላለም ወርቃገኘሁ ‹‹ከተደበቀበት›› ወጥቶ የአደባባይ ሰው እየሆነ ነው፡፡ ግፉንም በአደባባይ እየቀመሰው ነው፡፡ በሀገሩ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን በደልም ከማዕከላዊ እስከ የፍርድ ቤት ሂደቶች በተግባር እያየው ይገኛል፡፡ አሁን ዘላለም  ያስባል፤ መብትን ባለማስረገጥ እምቢተኝነቱ መጎልበት ያልማል፡፡ ወደፊት ምን ታስባለህ ሲባልም፣ ‹‹ይሄ ሁሉ በደል ባለባት ሀገር ትግሉ ወደፊት ብቻ ነው መራመድ ያለበት፣ እኔም ወደኋላ አልልም›› ይላል፡፡

[Google]