ቦርዱ ለኢትዮፒካሊንክ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

0
808

21 Jul 2015

አዲስ አበባ ሐምሌ 14/2007 የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ቦርድ በዛሚ ኤፍ ኤም 90 ነጥብ 7 ሬዲዮ ጣቢያ የሚተላለፈው የኢትዮፒካሊንክ “የውስጥ አዋቂ” ፕሮግራም ላይ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

ቦርዱ በየሣምንቱ ቅዳሜ ምሽት የሚሰራጨው “የውስጥ አዋቂ” ፕሮግራም ታርሞና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለህዝብ እንዲቀርብ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ዛሚ ኤፍ ኤም 90 ነጥብ 7 ሬዲዩ ጣቢያም ውሳኔውን ተቀብሎ እንዲያስፈጽምና ውሳኔው ተግባር ላይ መዋሉን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን እንዲከታተልም ቦርዱ ኃላፊነቱ ሰጥቷል።

ፕሮግራሙ የተሰጠውን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተቀበሎ የማያስተካክል ከሆነ ቦርዱ ተጨማሪ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ ሬዲዮ ጣቢያው በሚያሰራጨው ኢትዮፒካሊክ ፕሮግራም ላይ ‘ፈጽሟል’ ያለውን የሕግ ጥሰትና ውሳኔዎቹን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት “ሬዲዮ ጣቢያው በኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም በተለይም በሥሩ በሚያሰራጨው የውስጥ አዋቂ ፕሮግራም በግለሰቦች ላይ የስም ማጥፋት ፈጽሞ ጉዳዩ በቦርድ ሲታይ ቆይቷል።”

ባለሥልጣኑ በግለሰቦቹ በቀረበለት ቅሬታና በፕሮግራሙ ስህተት ላይ ተመስርቶ ቀደም ሲል ማስጠንቀቂያና ጊዜያዊ እግድ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውሰዋል።

ጣቢያው እግዱ እንዲነሳለት ለባለሥልጣኑ ቦርድ ባቀረበው አቤቱታ መሰረት ቦርዱ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠቱን ገልጸዋል።

ቦርዱ ጉዳዩን በመመርመር በባለሥልጣኑ ተወስኖ የነበረው የእግድ ቅጣት ተነስቶ ፕሮግራሙ ታርሞ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለህዝብ እንዲቀርብና ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ የህግ ጥሰት እንዳይፈጸም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ነው የተናገሩት።

“የውስጥ አዋቂ” ፕሮግራም በግለሰቦች ላይ በፈጸመው የስም ማጥፋት ተግባር ግለሰቦቹ ጣቢያው ድረስ በመምጣት ለህዝቡ መልስ እንዲሰጡ ባለሥልጣኑ ለጣቢያው ጥያቄ አቅርቦ ተግባራዊ አለመደረጉንም ጠቅሰዋል።

ቦርዱ የግለሰቦቹ መልስ የመስጠት መብት እንዲከበርና ፕሮግራሙ የግለሰቦቹን መልስ በተመሳሳይና በተመጣጣኝ ጊዜ ውስጥ እንዲያሰራጭ ውሳኔ ሰጥቷል ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።

ዛሚ ኤፍ 90 ነጥብ 7 ሬዲዮ ጣቢያ በተሰጠው ውሳኔ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ የቀረበለትን ጥያቄ ለጊዜው ሳይቀበለው ቀርቷል።

– See more at: http://www.ena.gov.et/index.php/social/item/6407-2015-07-21-23-35-18#sthash.XweqG3Rg.dpuf

[Google]