አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ሊመጡ ነው

0
924

Feb. 04, 2015

የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ወደ አገር ቤት ተመልሰው እንዲሠሩ በሕግ ያለመጠየቅ ጥበቃ በማግኘታቸው ምክንያት፣ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለሱ ተረጋገጠ፡፡

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለጹት፣ አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት የሚመለሱት መንግሥት በሕግ ያለመጠየቅ ጥበቃ ስለሰጣቸው ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ጥበቃው የተሰጣቸው ከአገር ከወጡ በኋላ ከመንግሥት ጋር ባደረጉት ረዥም ጊዜ የፈጀ ድርድር ሲሆን፣ ከተመለሱ በኋላም አከናውናቸዋለሁ ባሉዋቸው ሥራዎች ላይ መግባባት ላይ መደረሱን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት የሚመለሱት በዋናነት በጅምር የቀሩ የአክሰስ ሪል ስቴት የቤት ግንባታዎችን በማጠናቀቅና አዳዲስ ግንባታዎችንም በማከል ለቤት ገዥዎቹ ለማስረከብ በሚል እምነት ነው፡፡ ለዚህም የሥራ ክንውኑን የሚያመለክት ዝርዝር ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ለመሥራት እንዲችሉ መንግሥት በሕግ ያለመጠየቅ ጥበቃ እንዲሰጣቸው ካቀረቡት ጥያቄ ጐን ለጐን፣ ለማከናወን ያቀዱትን በዝርዝር አቅርበው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ለማስቻልም ሕጋዊ ከለላ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሠረት፣ ይኼው ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱን የሚጠቁሙት ምንጮች፣ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመጡ አስታውቀዋል፡፡ ትክክለኛውን ቀን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያካሂዱም የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ጉዳዩን በግልባጭ እንዲያውቁት ከፍትሕ ሚኒስቴር በደብዳቤ የተገለጸላቸው መሆኑን ምንጮች ጨምረው አስረድተዋል፡፡

አክሰስ ሪል ስቴት ከገባበት ቀውስ ለመውጣት በመንግሥት ደረጃ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ እንዲዋቀር ተደርጐ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ መንግሥት ይሁንታ ከመስጠቱ በፊትም መፍትሔ አፈላላጊው የቴክኒክ ኮሚቴ ከአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ለመግዛት ውል ከፈጸሙ ቤት ገዥዎች ጋር በመወያየት፣ በሪል ስቴቱ ጉዳይ መንግሥት የያዘውን አቋምና ዕቅድ አብራርቶ ነበር፡፡

ቤት ገዥዎቹ ቤታቸውን ለማግኘት እንዲችሉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንዳወጣ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ አቶ ኤርሚያስም በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ሥራውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይፈለጋል፡፡ ሆኖም አቶ ኤርሚያስ ባይመጡ እንኳ መንግሥት በተለያየ ደረጃ ባስቀመጠው ዕቅድ መሠረት ሥራውን ለማከናወን የሚችል መሆኑን ገልጾ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

የአክሰስ ሪል ስቴትን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል አቅም መኖሩን፣ በመንግሥት እንዲቋቋም የተደረገው የቴክኒክ ኮሚቴም አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ከመፈቀዱ በፊት ባደረገው ጥናት፣ አክሰስ ሪል ስቴት በስሙና በሌላ ወገን የሚገኙ መሬቶች እንዳሉትና ግንባታዎችን ለማካሄድ የሚያስችል አቅም እንደሚኖረው ታውቋል ተብሏል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት ይመጣሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥበትም፣ ይመለሱ የሚለው ይሁንታ በመገኘቱ በዚህ መሠረት መጥተው ወደ ሥራ ከገቡ የተፈጠረውን ክፍተት ይሞላሉ ተብሎ ታምኖበታል፡፡ እሳቸውም በቀጥታ ወደ ሥራ ገብተው የተፈጠረውን ችግር በማስወገድ፣ የቤት ደንበኞችን ፍላጎት እንደሚያሳኩ እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔም በአክሰስ ሪል ስቴት የተፈጠረውን ችግር መንግሥት የሚፈታው መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ችግር የማይፈታ ከሆነም የአገሪቱ የአክሲዮን ኩባንያዎች የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ጉዳት ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ሐሳብ መሰንዘራቸው፣ የአክሰስ ሪል ስቴትን ችግር ለመፍታት መንግሥት ትኩረት መስጠቱን የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡

ከአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ለመግዛት የተዋዋሉ ቤት ገዥዎች ሁለት ሺሕ እንደሚጠጉ ይገመታል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዱባይ ከተማ የሚገኙ ሲሆን፣ ወደ አገር ቤት ሲመለሱ በጥበቃው መሠረት በተለያዩ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ከቀረበባቸው ክስ ነፃ ሆነው የጀመሩትን የሪል ስቴት ሥራ ከዳር እንደሚያደርሱ ይጠበቃሉ፡፡

 Source:: Ethiopian Reporter

– See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/4342#sthash.xOEsyaPn.dpuf

[Google]