በኢትዮጵያ 6 ሚሊየን ሕዝብ ስር በሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ነው ተባለ

0
915

ጥር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-እ.ኤ.አ በ2013 ለሁለተኛው አጋማሽ ማለትም ከጁላይ እስከ ዲሴምበር የአስቸኩዋይ የእለት ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልገው 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሕዝብ የሚውል 162 ሺህ176 ሜትሪክ ቶን ምግብ ውስጥ ማሙዋላት የተቻለው 69 በመቶ ያህሉን ብቻ መሆኑን፣ 6 ሚሊየን ያህል ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ቤተሰቦች በሴፍትኔት መታቀፋቸውን የግብርና ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ዛሬ በፓርላማ ባቀረቡት የመ/ቤታቸው የስድስት ወራት ስራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው በድርቅ ችግር ውስጥ ላለው ወገን የሚያስፈልገው የምግብ መጠን እና አቅርቦቱ መካከል ክፍተት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የሴፍቲኔት ፕሮግራም ባለባቸው ወረዳዎች የተያዘው የመጠባበቂ በጀት በመጠቀም ቀሪው አቅርቦት እንዲሟላ ተደርጎአል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ባለፉት ስድስት ወራት ከግጭት እና ከጎርፍ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው 1 ነጥብ 5ሚሊየን ሕዝብ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታ ለመስጠት ታስቦ ለ245 ሺህ 385 ሕዝብ  ብቻ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ኣመቱ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ህዝብ ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን ወገኖች በልማታዊ ሴፍትኔት ለማሳተፍ ታቅዶ 6,ሚሊዮን 3 ሺ 551 ቤተሰቦች በፕሮግራሙ ማሳተፍ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ከአፋርና ሶማሌ ክልሎች 32 አዳዲስ ወረዳዎች በፕሮግራሙ በመካተታቸው ነው ብለዋል፡፡

ከድርቁ ጋር በተያያዘ ለቤተሰብ ጥሪት ግንባታ በየወረዳው የሚሰጠው ብድር በወቅቱ ተመልሶ ለቀጣይ ብድር አገልግሎት ማዋል ያለመቻል፣ተጨማሪ ብድር በሚፈለገው መጠን ያለማቅረብ፣በአንዳንድ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ ተጠቃሚዎች እንዳያንሰራሩ ማድረጉ፣በአመራሩም ሆነ በባለሙያው በቂ ድጋፍና ክትትል ያለማድረግ የሚሉትን በችግርነታቸው አንስተውታል፡፡

ኦክስፋም በቅርቡ ባስጠናው ጥናት ኢትዮጵያ ከቻድ በመቀጠል በአለም ላይ ከፍተኛ የምግብ ችግር ከሚታይባቸውና ዜጎቻቸውም ጥራት ያለው ምግብ ከማይመገቡባቸው አገራት ተርታ ፈርጇታል።

Source : Ethsat.com

[Google]