ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የተመለሱ የትግራይ ክልል ተወላጆችን በተለያዩ የስራ መስኮች ለማሰማራት ዝግጅት እየተደረገ ነው

0
815

መቀሌ ህዳር 30/2006 ከሰውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የተመለሱ ዜጐችን በተለያዩ የስራ መስኮች ለማሰማራት ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የወጣቶች ብቃት ማሳደግ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ሃይሉ እንደገለጡት በመንግስት ጥረት እስካሁን ወደ አገራቸው ከተመለሱ ስደተኞች መካከል ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑት የትግራይ ክልል ተወላጆች ናቸው፡፡ ከእነዚሁ ዜጐች መካከልም ከ16 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ክልሉ ገብተዋል። መንግስት ስደተኞቹን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ከማድረግ ጀምሮ የማቋቋሚያ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ የክልሉ መንግስትም ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ የተጀመረው ጥረት እንዲጠናከር ማድረጉን አስረድተዋል። ከስደት ተመላሾቹ ወደየአካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላ ተደራጅተው መሰመራት የሚፈልጉትን የስራ መስክ ማእከል ያደረገ ስልጠና እንደሚሰጣቸውና ብድርና ሌሎች ድጋፎች እንዲያገኙ ሁኔታዎች መመቻቸቱን አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል። ከተዘጋጁት የስራ አማራጮች መካከል በገጠር ልማት ተራራማ ቦታዎች የማልማትና በማእድን ሃብት፣ በእንስሳት ሃብትና በመስኖ ልማት፣ በከተማ ልማትም በድንጋይ ንጣፍ፣ በተለያዩ የእደጥበብ ውጤቶችና የከተማ ግብርና በሚሉት ተለይተው እንዲዘጋጁ መደረጉን ኃላፊው ገልጠዋል። ወጣቶቹ በውጭው አለም የነበረውን ሁኔታ አይተው በመምጣታቸውና በአገራቸው ያለውን የስራ አማራጮች መስፋታቸው ስለሚረዱ በተዘጋጁላቸው የስራ መስኮች በስፋት ሊሰማሩ እንደሚችሉ አቶ ሙሉጌታ ያላቸው እምነት ገልፀዋል። ከስደት ተመላሾቹ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱና ወደ ልማት እንዲገቡ የሚያደርጉ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው በስራ ላይ ሲሆኑ በአዲስ አበባም ጽህፈት ቤት ተከፍቶ ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያዎች መመደባቸው ከአቶ ሙሉጌታ ማብራሪያ ለመረዳ ተችሏል።

Source: ENA

[Google]