ጥላዬ ያሉት ሲጥል

0
824

በአሸናፊ ኃይሌ

በኢትዮጵያውያን ዘንድ የጋብቻም ሆነ የሥጋ ዝምድና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሕግም ድጋፍ ያለው ነው፡፡ ‹‹ ትምህርት እስከ ስምንት ዘመድ እስከ አክስት›› የሚለው የግብዞች አባባል ቦታ የለውም፡፡ ሕብረተሰቡ ክብር ሰጥቶ የገነባው የሥጋ ዝምድና አጥር በአንዳንድ ግለሰቦች ሲጣስ በሕግ በኩል አስፈላጊው የጥፋተኝነት ውሣኔ ይወሰንባቸዋል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ቱላ ክፍለ ከተማ ውስጥ የተፈፀመው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በሥጋ ዝምድና በተሳሰሩ ሰዎች መካከል መሆኑ ጉዳዩን አፀያፊ ቢያደርገውም ወንጀሉ የተፈፀመው ምንም በማታውቅ የ15 ዓመት ታዳጊ ሕፃን መሆኑ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ መስከረም 18 ቀን 2006 ዓ.ም በክፍለ ከተማው ሀረንፋማ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው መንግሥቱ ማርሣ ወደ ቱላ ከተማ ለመሄድ ሲነሳ ያጎቱ ልጅ የሆነችው ሕፃን አብራው እንድትሄድ ያደርጋል፡፡ ቤተሰብም የምትሄደው ከአጎቷ ልጅ ጋር በመሆኑ ምንም ሥጋት ሳይገባቸው እንዲህ ትሆናለችም ብለው ሳይጠረጥሩ ቦታ እንድታውቅ ሀገር እንድትለምድ በማለት ጥያቄዋን ተቀብለው ይፈቅዱላታል፡፡ በሕፃኗም አእምሮ የተቀረፀው ከገጠር ወጣ ብላ ከተማ ውስጥ በምታየው ነገር መደሰቷን እንጂ ሌላ ጣጣ ይመጣብኛል የሚል ግምት አልነበራትም፡፡ በእርሷ ላይ ክፉ ነገር ቢመጣም እንኳን አለኝታዬ የምትለው እንደ ወንድም  የምትቆጥረው የአጎቷ ልጅ አለላት፡፡ ከወንድሟ ጋር ሆና ለምን ትጨነቅ ለምንስ ትሥጋ አብሯት ባለው ሰው እምነቷን ጥላለች፡፡ ከዚህ ሰው ጋር በመንገድ እያወሩ ቱላ ከተማ ሲደርሱ የፀሐይዋ ግለት ስለጨመረ የቀኑን ሙቀት ከጓደኛው ቤት ማሳለፍ እንዳለባቸው የሕጿናን ፈቃድ ጠየቀ፡፡

እርሷም በመንገዱና በሙቀቱ ተዳክማ ስለነበረች ሃሳቡን መልካም ነው ብላ ተቀበለች፡፡ ወደ ጓደኛው ቤት ይዟት ሲሄድ ጓደኛውም  አስቸኳይ ሥራ እንዳለበት ነግሮ የቤቱን ቁልፍ ሰጥቷቸው ይሄዳል፡፡ በቤቱ ውስጥ ያሉት የ15 ዓመቷ ሕፃንና ይዟት የመጣው ዘመዷ ብቻ ነበሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ወንድምነቱ ተረስቶ፣ ዝምድናው ተዘንግቶ ሊፈጽመው ያሰበው ነገር በቃላት ለመግለፅ የሚያሰቅቅ ነው፡፡ ይህን ያደርጋል ብላ ባልገመተችው ሕፃን ላይ የወንድነት ጉልበቱን ተጠቅም የሕፃን ገላዋን አስገድዶ ክብረ ንጽህናዋን ይወስዳል፡፡ ሕፃኗ በደረሰባት ጥቃት ተደናግጣ ባሰማችው የድረሱልኝ ጩኸት የተሰባሰቡት የአካባቢው ነዋሪዎች የደረሰባትን ጥቃት ለፖሊስ የሳውቃሉ፡፡ ይህ ጥቆማ የደረሰው ፖሊስም ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር በማዋል ሕፃኗ የሕክምና እርዳታ እንድታገኝ ወደ ጤና ተቋም ላኳት፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ የሰው ምስክርና የሕክምና ማስረጃ አሰባሰቦ በተጠርጣሪው ላይ ክስ በመመስረት ለሚመለከተው የፍትህ አካል መዝገቡን አቅርቦ እንዲመለከተው አድርጓል፡፡ ይህን የክስ መዝገብ የተመለከተው የሐዋሳ ከተማ ቱላ ምድብ ችሎት በተከሳሽ መንግሥቱ ማርሣ ላይ የቀረበው ማስረጃ ጥፋተኛ ነው ለማለት በቂ ሆኖ ስላገኘው ጥቅምት 8 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ነው ያለውን መንግሥቱ ማርሣን በ13 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የወሰነበት መሆኑን ሪፖርተር አይናለም ፍቃዱ በቦታው ተገኝታ ዘግባለች፡፡

ምንጭ ፖሊስ እና እርምጃው

[Google]