ሙዚቃውን ቀንስ አልቀንስም በሚል ፀብ አከራዩን የገደለው በእስራት ተቀጣ

0
888

ተስፋሁን ብርሃኑ

ነሐሴ 1 ቀን 2005 ዓ.ም

ፖሊስና ርምጃው

ሙዚቃውን ቀንስ አልቀንስም በሚል ፀብ የ3ዐ ዓመቷን የቤት አከራይ በሳንጃ አንገቷን ወግቶ የገደለው ተከራይ በ18 ዓመት እስራት ተቀጣ፡፡ ወንጀሉ የተፈፀመው በ15/6/2ዐዐ4 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡3ዐ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 2ዐ ልዩ ቦታው እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ ተሾመ ብርሃኑ የተባለው ወንጀለኛ ከሟች መሰሉ ደጉ ቤት ተከራይቶ የኖረ ሲሆን ሙዚቃ ከፍ አድርገህ ከፍተሀል በሚል ፀብ ምክነያት ሙዚቃውን ቀንስ ስትለኝ እምቢ ስላት ቆጣሪውን አጠፋችብኝ ብሏል፡፡ በጣም ተናድጄ ለምን ታጠፊብኛለሽ ስላት እኔ ምን ላድርግህ ብላ በያዘችው መጥረቢያ ጭንቅላቴን ስተመታኝ ሽንኩርት ስከትፍበት በነበረው ሳንጃ አንገቷ ላይና ማጅራቷን ወግቼ ገድያታለሁ ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን በምርመራ ወቅት ተናግሯል፡፡ ወንጀለኛው ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላ ሊያመልጥ ሲል በአካባቢው ኅብረተሰብ ትብብር ተይዞ ወንጀሉን የፈፀመበትን ሳንጃ ከደበቀበት ጫካ በመምራት አሳይቷል፡፡

የጉዳዩ ወንጀል መርማሪ የሆኑት ምክትል ሳጅን ታፈሰ ዘበርጋ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ካሰባሰቡ በኋላ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልከዋል፡፡ የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሲከታተል ከቆየ በኋላ ተሾመ ብረሃኑ ሟች መሰሉ ደጉን ሆን ብሎ የገደላት መሆኑን በማረጋገጡ የ18 ዓመት እስራት በይኖበታል፡፡ በመጨረሻ በአከራይና በተከራይ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባውና እንደዚህ አይነት ቀላል አለመግባባት ሰላም በመነጋገር መፈታት በአሰቃቂ ሁኔታ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡

[Google]